”የቤተሰብ ሚና ለትውልድ ስብዕና” የዓለም የቤተሰብ ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።

ዓለማቀፉ የቤተሰብ ቀን በዓለም ለ30ኛ በሀገራችን ለመጀመርያ ጊዜ በዛሬው ዕለት በድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ የቤተሰብን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ለማሳደግ ፣ ለችግር የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማሰብና ለመደገፍ ፣ የቤተሰብ አባላት ምስጋናና ክብር የሚሰጣጡበትና ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ”ቤተሰብ የማህበረሰብ መሠረትና የሀገር መሠረት በመሆኑ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል” ብለዋል።

ቤተሰብ አምራች ሲሆን አገር ምርታማ ትሆናለች ያሉት ክብርት ሚንስትሯ ሀገር እንድትፀና የቤተሰብ ሁለንተናዊ ደኅንነት እና ዘላቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባው ገልጸዋል።

አክለውም ቤተሰብ የትውልድን ስብዕና ለመገንባት ወሳኝ መሰረት በመሆኑ ለቤተሰብ መሠረት መጠናከር ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

የሴቶችና መህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሼቴ በበኩላቸው መንግሥት የቤተሰብን ደኅንነትና ምርታማነት ለማስጠበቅ ትኩረት በመሥጠት ፖሊሲዎችና መዋቅሮችን ወደ ሥራ በማስገባት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ቤተሰብ በመልካም ስብዕና የታነፀ ትውልድ የሚተካበት ፣ ምርትና አገልግሎት ለቤተሰቡ የሚቀርብበት የቤተሰቡ አባላት ፍቅርና እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚገኙበት ተቋም መሆን ይገባዋል ተብሏል።

የትምህርት ተቋማትና መገናኛ ብዙኀን በግብረ ገብነት ላይ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ የሥነ ህዝብና የቤተሰብ ፖሊሲዎችና የቤተሰብ ጉዳይን የተመለከቱ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *