በሴቶችንና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጥቃቶችን በመከላከልና በማስቆም ረገድ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን አቅም ለማጎልበት ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው

(አዳማ፣ ግንቦት 22/2015 ዓ.ም) በሴቶችንና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጥቃቶችን በመከላከልና በማስቆም ረገድ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን አቅም ለማጎልበት ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል።

ስልጠናው የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ሴቶችንና ህጻናት የተመለከቱ ጉዳዮችን በተለይም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጥቃቶችን መከላከልና ማስቆም ላይ ያተኮሩ ይዘቶችን በፕሮግራማቸው አካተው መተግበር በሚችሉበት አግባብ ላይ ያላቸውን ግንዛቤና ሚና ለማጎልበት ያለመ እንደሆነ የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ ተናግረዋል።

የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ካላቸው ሰፊ ተደራሽነት አኳያ ጠቃሚ መልዕክቶችን በመቅረጽ ህብረተሰቡ ሊገነዘበው በሚችል መንገድ በማስተማር፣ ጎጂ ድርጊቶች እንዲወገዱ ጠቃሚ ባህሎች እንዲጎለብቱ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩና የበኩላቸውንድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን መሰረታዊ የባህሪና የአመለካከት ለውጥ በማምጣት እንደየአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ለሚያደርጉት ጥረት ስኬታማነት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው ባለስልጣኑ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን በየአካባቢው እንዲስፋፉ ሲያደርግ ከተሰጣቸው ተልዕኮ መካከል አንዱ ሴቶችንና ህጻናት የተመለከተ ፕሮግራሞችን እንዲቀርጹ፣ በሚያሰራጩት ፕሮግራሞች ውስጥ ድምጻቸውን እንዲያስተጋቡና ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በመሆኑ ተልኳቸውን በሚገባ እንዲወጡ አሳስበዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጋራ መግባቢያ በመፈራረም በተቀናጀ፣ በተደራጀና በተሳሰረ መልኩ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ስልጠናው በተለይ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ጾታን መሰረት ያደረጉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ ያላቸው አስተዋጽኦ፣ የሴቶችንና ህጻናትን ጉዳይ ተደራሽ የማድረጊያ ዘዴዎች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ ሌሎች አማራጭ የዘመናዊ ዲጂታልየመገናኛ አውታረ መረቦች አጠቃቀም ላይ ትኩረት ያደረጉ እንደሆኑ በመድረኩ ተጠቁሟል።

በስልጠናው ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የማህበረሰብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጆችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *