በአይነቱ ልዩ የሆነ የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ

(በአዲስ አበባ፣ ግንቦት 30/ 2015 ዓ.ም) በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት እና በማሌሳ ኤቨንት ሀሳብ አመንጭነት ከሰኔ 7-9 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆይና ሴቶች በስራ ፈጠራ፣ በአምራችነት፣ በንግድ፣ በገበያ ትስስር፣ በኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት እና ተወዳዳሪነት ዙሪያ ያላቸውን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያሰፋ በአይነቱ ልዩ የሆነ የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
ሊካሄድ የታቀደውን ኤክስፖ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል ለሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን በመግለጫው የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ እንደተናገሩት፤ በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሆኖም አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሴት ስራ ፈጣሪዎች፣ አምራቾች፣ የንግድ ተቋም ባለቤቶች እና መሪዎች ከብድር አቅርቦት፣ ከወለድ ምጣኔና ከእፎይታ ጊዜ፣ ዘላቂ የገበያ ትስስር ከመፍጠር፣ ከምርት ማቀነባበሪያና ማሳያ፣ ከመስሪያ ቦታ፣ ከቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ስልጠናዎችን ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው አንስተዋል።
ይህም ባሰቡት ልክ እና ፍጥነት ተቋሞቻቸውን እንዳያሳድጉና በድካማቸው ልክ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማነቆ ሆኖባቸው መቆየቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየታየ ያለውን አበረታች ውጤትና የለውጥ ጅማሮ በሁሉም ዘርፎች ፍትሃዊነትና ዘላቂነት ባለው መልኩ አጠናክሮ ለማስቀጠል እና የሴቶችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ሆኖም ከችግሩ ስፋት አኳያ በመንግስት ብቻ በሚደረግ ጥረት የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ አዳጋች በመሆኑ የልማት አጋራት፣ የግል ባለሃብቶች እና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች በትብብር እንዲሰሩ በአጽዕኖት አሳስበዋል።
ማሌሳ ኤቨንት ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ነጋዴ ሴቶች የሚሳተፉበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ኤክስፖ እንዲዘጋጅ ላሳየው ተነሳሽነት እንዲሁም በአጋርነት ከድርጅቱ ጋር እየሰሩ ያሉ የፌዴራል ተቋማትን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በተጠቃሚ ሴቶች ስም ከልብ አመስግነዋል።
“Connect, Create, Accelerate” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ኤክስፖ ከ100 በላይ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ሴት ስራ ፈጣሪዎች፣ አምራቾች እና የንግድ ተቋም መሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው በመቅረብ ከ35 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች እንደሚሸጡና እንደሚያስተዋውቁ የማሌሳ ኢቨንት ስራ አስኪያጅ ሰላማዊት ደጀን ገልጸዋል።
እንደስራ አስኪያጇ፤ በኤክስፖው ምርት ከመሸጥና ማስተዋወቅ ጎን ለጎን የፓናል ውይይት የሚካሄድ እና ከንግድ ስራ ጋር የተያያዘና ጊዜውን የዋጀ ስልጠና እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ስኬታማ የሆኑ ሴቶች ልምድና ተሞክሯቸውን እንደሚያካፍሉ ይጠበቃልም ብለዋል።
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *