“ሴትን ከጥቃት መከላከል ሀገርን ከውድቀት መታደግ ነው” ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ

<<ጽጌረዳ ጫንያለው>>

በዓለም ጤና ድርጅት አዲስ ትንታኔ መሠረት በዓለም
አቀፍ ደረጃ ከሦስት ሴቶች መካከል አንዷ በሕይወቷ
ውስጥ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባታል።
በዚህ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት እድሜያቸው
15 እና ከዚያ በላይ የሆኑ 736 ሚሊዮን ያህል ሴቶች
ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው፤ እኤአ በ2013 የዓለም
የጤና ድርጅት ከሠራው ጥናት ወዲህ የተጎዱ ሴቶች
ቁጥር በአብዛኛው ባይለወጥም ይሄኛው ግን ጥቃት
የሚጀምረው ገና በልጅነት መሆኑን አመልክቷል።
በዚህም መሰረት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት
ከሆኑት አራት ሴቶች መካከል አንዷ ዕድሜዋ እስከ
ሃያዎቹ አጋማሽ እስኪደርስ በቅርብ አጋሯ ጥቃት
ይደርስባታል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው፤ ከ2000
እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ከ161 አገራት የተገኘውን
መረጃ በመተንተን እነዚህን አዳዲስ ግኝቶች ለማውጣት
ችሏል፡፡ ጥናቱ በኮቪድ -19 ወረርሽኝ የተገኘ መረጃን
አላካተተም፡፡ ስለዚህም በመረጃው መሰረት በቅርብ
ባልደረባ የሚደርስ ጥቃት በጣም የተስፋፋ ዓለም አቀፍ
የጥቃት ዓይነት ሆኗል።
ስድስት በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ባለቤታቸው ወይም
አጋራቸው ባልሆነ ሰው ጥቃት እንደሚደርስባቸው ጥናቱ
ያስረዳል፡፡ “በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በዓለም
አቀፍ ደረጃ እንደወረርሽኝ የህብረተሰብ ችግር ሆኗል።
ጥቃቱ የሚጀምረውም ገና በለጋ ዕድሜ ላይ በሚገኙ
ሴቶች ነው፡፡ መገለልን በመፍራት ብዙ ሴቶች ወሲባዊ
ጥቃትን ሪፖርት እንዳያደርጉ እንቅፋት ሊሆን ስለሚችል
ቁጥሩ የበለጠ ሊጨምር ይችላል” ሲሉ የጥናት ጸሐፊ
ዶክተር ክላውዲያ ጋርሲያ-ሞሬኖ ለቢቢሲ መናገራቸውን
ቢቢሲ ባወጣው መረጃ አስፍሮታል።
ሴቶች የበለጠ ለጥቃት የሚጋለጡት በተለይም
በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ በአካባቢያቸው ባሉ
አካላት ሲሆን፤ ለአብነትም በቤተሰብ አካልና በቅርብ
ባልደረባቸው ይሆናል፡፡ በቢቢሲ መረጃ መሰረት
በእነዚህ ሀገሮች ውስጥ ከሚኖሩት ከአራት ሴቶች አንዷ
(37 በመቶ) ጥቃት ይደርስባታል። በአውሮፓ (16-23
በመቶ) እና በማዕከላዊ እስያ (18 በመቶ) ለሚኖሩ ደግሞ
ይህ ከአምስት ሴቶች ወደ አንድ ዝቅ ይላል፡፡ ይህ ማለት
ደግሞ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በተወሰኑ ሀገራት
ላይ ብቻ ያለ ሳይሆን በሁሉም ሀገሮች እና ባህሎች ውስጥ
ተንሰራፍቶ የሚገኝ ነው።
ተግባሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶችን እና
ቤተሰቦቻቸውን የሚጎዳ ሲሆን፤ በኮቪድ -19 ወረርሽኝ
ምክንያት ተባብሶ ነበርም። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ
ደግሞ ቤት የሚያሳልፈው ሰው መበራከቱ ነው።
ይሁን እንጂ ከዚያም በኋላ ወጣ ገባ በሆነ መልኩም
ቢሆን የሚሰሙ ዜናዎች በርካታ ሴቶች የተለያዩ ጥቃት
እንደሚደርሱባቸው አስረጂ ናቸው፡፡ በቅርቡ እዚሁ
ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን በመገናኛ ብዙኃን ሲዘዋወር
የነበረን አንድ ጉዳይ ለአብነት መመልከት ይቻላል።
ብዙዎች በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት ነገር አለ እንዴ
ያስባለው ክስተት ነገሩ እንዲህ ነው የሆነው፣ ጥቃት
ደርሶባታል የተባለችው ግለሰብ ወይዘሪት ፀጋ በላቸው
ትባላለች፡፡ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ እና የዳሸን ባንክ ባልደረባ
ስትሆን፤ በቀን 15/9/2015 ዓ.ም ከስራ ወጥታ ወደ ግል
ጉዳዩዋ አመራች፡፡ በተለምዶ አሮጌው መናኸሪያ ተብሎ
በሚጠራው አካባቢ ስትደርስም ያልጠበቀችው ነገር
ሆነ። በመግለጫው እንደተገለጸው፤ በሀዋሳ ከንቲባ የግል
ጠባቂ ጠልፋ ተፈጸመባት፡፡ የክፍለ ከተማው ፖሊስ
መምሪያም ይህንን ማረጋገጥ ቻለ፡፡ ለሕዝብም ይፋ
አደረገው፡፡ ሁሉም እርሷን ለማግኘት ርብርብ ማድረግ
የጀመረው ከዚያ በኋላ ነበር፡፡
በአንድ በኩል ከንቲባ ጽህፈት ቤት በሌላ በኩል
ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲሁም የጸጥታ አካላትና
ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተፈጸመውን
ድርጊት አውግዘው መግለጫ አወጡ፡፡ ማድረግ
ያለባቸውንም ነገር ወደ ማድረጉ ገቡ፡፡ ምክንያቱም
ጠለፋ ከግለሰብ ፈቃድ ውጭ በኃይል የሚፈጸም፣
እጅግ አስነዋሪ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ህገወጥ
ድርጊት ከመሆኑም በላይ ዜጎች በዓለምና ሀገር አቀፍ
ደረጃ የተቀመጡ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በእጅጉ
የሚጻረር ነው፡፡
ይህ ነገር ምንን ያመለክታል ከተባለ እንደሀገር
የተሰራው ሥራ አናሳ መሆኑን ነው፡፡ ዛሬ ሰለጠንን
በተባለበት ወቅት ሴትን ልጅ ጠብቆ መጥለፍ እጅግ
አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ እናም ብዙ መስራት እንደሚስፈልግ
ድርጊቱ ያሳስበናልና ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
ብዙ ስራዎች እንዳሉበት አምኖ ወደ ተግባር መግባቱን
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ባወጣው መግለጫ ገልጸዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደነዚህ
አይነት ድርጊቶችን በተለያየ መልኩ ከተለያዩ
ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ይሰራል፡፡ ለምሳሌ፡-
የወይዘሪት ፀጋ ጉዳይን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ
እንዳስቀመጠው፤ ድርጊቱ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መረጃ በመለዋወጥ
ተገቢው ፍትህ እንዲተገበር ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ
በፖሊስና በሕዝብ ትብብር አሁን ተበዳይ በሰላም ወደ
ቤተሰቧ ተመልሳለች። ቢሆንም የወንጀል ተጠርጣሪውና
ተባባሪዎች ላይ የሚደረገው ክትትል ተጠናክሮ
የሚቀጥል ሲሆን፤ የጠለፋ ወንጀል ድርጊቱ ተገቢውን
የፍትሕ ውሳኔ አግኝቶ ለሌሎች ማስተማሪያ እንደሚሆን
በፅኑ ይታገላል።
የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ተፈፀመ የተባለውን
የወንጀል ድርጊት መሰረት በማድረግ ተጠርጣሪውን
በቁጥጥር ስር ለማዋልና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸወ አካላት
ጋር ይሰራል። በዚህ አጋጣሚ በሴቶች መብት ዙሪያ
የሚሰሩ ተቋማትን ጨምሮ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው
እየተንቀሳቀሱ ለሚገኙ የክልል ቢሮዎች እና የፍትህ
አካላት በሙሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አድናቆቱን
ይገልፃል።
በሌላ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም
“ሴትን ከጥቃት መከላከል ሀገርን ከውድቀት
መታደግ ነው”
ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል መረጃውን ለሕዝብ ይፋ
የሚያደርግ መሆኑን እያስታወቀ፤ የተበዳይ ቤተሰብም
እና ተበዳይ እንዲሁም ህብረተሰቡ ውጤቱን በትዕግስት
እንዲጠባበቁ በአክብሮት ይጠይቃል። ይህ ጉዳዬ
የየአንድ ቀን ሥራ አይደለም፡፡ ክትትልና ሌሎች ላይ
እንዳይፈጸም ማድረግን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም መስሪያ
ቤቱ ድርጊቱን ከማውገዝ አልፎ የተለያዩ ተግባራትን
እየከወነ ይገኛል፡፡ አንዱ በክልል ካሉ ተቋማት ጋር በጋራ
መስራት ሲሆን፤ ለአብነትም ከፍትህና ጤና ተቋማት ጋር
በቅርበት የሚሰራ ይሆናል፡፡
ሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች
እንዲቆሙ ለማድረግ በየጊዜው በተለየ መልኩ እንቅስቃሴ
እየተደረገ ሥራዎች ቢሰሩም የመከሰቻ አጋጣሚያቸው
ግን መልኩን እየቀየረ አሁንም ችግር ውስጥ እንዳለን
ያሳየናል። በጉዳዩ ላይ በስፋት የሚሰራውና ኃላፊነቱን
ወስዶ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ የሚያከናውነው
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግሩን ለመከላከል
እንደ ሀገር የማህበረሰቡ ርብርብ እንደሚያስፈልግ
በተደጋጋሚ ይገልጻል። ሆኖም በሴቶችና ሕፃናት ላይ
የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች ግን ቀንሰዋል ቢባልም
እምብዛም ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህም መስሪያ
ቤቱ ከሦስት ቀን በፊት ባወጣው መረጃ እንዳስቀመጠው፤
ከእነዚህ ተቋማት ጋር በማህበራዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ
ልምድ ልውውጥ እየተከናወነ ነው፡፡
አገር አቀፍ የጾታዊ ጥቃት መከላከልና ምላሽ
ሥራዎች ትብብርን፣ በጋራ መስራትን የሚጠይቁ
በመሆናቸው የጋራ ስራ እቅድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህም
ለውይይት የቀረበ ሰነድ ማለትም በሴቶችና ማህበራዊ
ጉዳይ ሚኒስቴር እየተዘጋጁ ያሉ High level intitative
የሆኑ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መከላከል እና ምላሽ
መስጠት ፖሊሲ፤ የጉዳይ አያያዝ case managnment፤
የአገልግሎት ምላሽ አስጣጥ ስታንዳርድና የፆታ ጥቃት
አድራሾች ምዝገባ ስርአት በመዘጋጀት ቀርቦ ውይይት
ተካሂዶበታል፡፡ ጥሩ ተጨማሪ የሚሆኑ ሀሳቦች
እንደተሰበሰቡበት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ
አለሚቱ ኡሞድ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደሚሉት፤ ሴትን ከጥቃት
መከላከል ሀገርን ከውድቀት መታደግ ነው፡፡ ስለሆነም
አገር አቀፍ የጾታዊ ጥቃት መከላከልና ምላሽ ሥራዎችን
ክልሎች በተቀናጀ መልኩ ሊያከናውኑ ይገባል። ሴቶችና
ሕፃናት ከጥቃት ነፃ ሆነው በትምህርት፣ በአመራርነት፣
በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ
መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ
መገናኛ ብዙኃን መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
ጊዜው ቴክኖሎጂ በመሆኑ ከሁሉም በላይ የመገናኛ
ብዙኃን ተሰሚነት የላቀ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይ
ማህበረሰብን እየገለገልን ነው የሚሉ መገናኛ ብዙኃን
ሴቶችንና ህጻናት የተመለከቱ ጉዳዮችን በስፋት ሊዘግቡና
ግንዛቤ ሊፈጥሩ ይገባል፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና
ጥቃቶችን መከላከልና ማስቆም የሚቻለውም በዚህ
መልኩ መረዳዳት ሲቻል እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ካላቸው ሰፊ
ተደራሽነት አኳያ ጠቃሚ መልዕክቶችን በመቅረጽ
ህብረተሰቡ ሊገነዘበው በሚችል መንገድ በማስተማር
ጎጂ ድርጊቶች እንዲወገዱ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ጠቃሚ
ባህሎችንም ለማጎልበት ሁነኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ለዚህ
ደግሞ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን መሰረታዊ የባህሪና
የአመለካከት ለውጥ በማምጣት እንደየአካባቢያቸው
ነባራዊ ሁኔታ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት
ለሚያደርጉት ጥረት ስኬታማነት አስፈላጊውን እገዛና
ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የሴት ልጅ ጥቃት የሴቷ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብ
ጥቃትም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ሴት እናት፣ እህት፣
ሀገርም ናትና፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *