የቻይና የንግድ ሥራ በአፍሪካ ለማህበራዊ ኃላፊነቶች ጥምረት በአፍሪካ ሊገነባ ካቀደው 1 ሺ መንደሮች ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ አስታወቀ።

(አዲስ አበባ፣ ህዳር 5/2016 ዓ.ም) የቻይና የንግድ ሥራ በአፍሪካ ለማህበራዊ ኃላፊነቶች ጥምረት ሥራ አስፈፃሚ ዲያዮ ቹንሄ የተመራ የልዑካን ቡድን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር መክሯል።

ጥምረቱ በአፍሪካ ውስጥ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በኢኮኖሚ እና ንግድ ትብብር ላይ በተሰማሩ የቻይና ኢንተርፕራይዞች በፈቃደኝነት የተቋቋመ ሲሆን በአፍሪካ የተለያዩ የማህበራዊ ኢኮኖሚ ድጋፎችን የሚያደርግ ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጥምረቱ ሊገነባ ካቀደው መንደሮች ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የቻይናና የኢትዮጵያን የጠበቀ ግንኙነት ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ የሴቶችና እና ህፃናት እንዲሁም የአጠቃላይ ማህበረሰቡን ህይወት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ እና ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት የቻይና መንግስት እና ኢንተርፕራይዞች እያበረከቱ ላለው አስተዋፅኦ አመስግነዋል።

የቻይና የንግድ ሥራ በአፍሪካ ለማህበራዊ ኃላፊነቶች ጥምረት ሥራ አስፈፃሚ ዲያዮ ቹንሄ ጥምረቱ ሊገነባ ካቀዳቸው 1ሺ መንደሮች ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

የሴቶችና ህፃናት የማህበራዊ ህይወት መሻሻል ላይ ጥምረቱ ይሰራል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ለፕሮጀክቱ መሳካት የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የቻይና የንግድ ሥራ በአፍሪካ ለማህበራዊ ኃላፊነቶች ጥምረት በአፍሪካ ውስጥ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በኢኮኖሚ እና ንግድ ትብብር ላይ በተሰማሩ የቻይና ኢንተርፕራይዞች በፈቃደኝነት የተቋቋመ ሲሆን በአፍሪካ ውስጥ ለማህበራዊ ህይወት መሻሻል ያግዛሉ ያላቸውን 1ሺ መንደሮችን ለመገንባት እየሰራ ነው።

Please follow and like us: