በሐረሪ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት በይፉ ተቋቋመ

በምስረታ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ እንደተናገሩት፤ ወጣቶች ካላቸው እምቅ አቅም፣ እውቀትና ክህሎት አንፃር ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት የወጣቶችን ችግሮች ለመፍታት፣ መብታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ህገመንግስቱንና ፖሊሲውን መሠረት በማድረግ በርካታ የወጣት አደረጃጀቶች ተቋቁመው የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናወኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ሆኖም በመንግስትና በሀገራችን ወጣቶች መካከል ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል፣ በወጣቶች የሚመራና ከመንግስት ጋር በመመካከር የሚሰራ፣ እውነተኛ የወጣቶች ድምፅ የሚሆን ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱን ወደታች በማውረድ በየደረጃው ማቋቋምና ስራ ማስጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም በመጀመሪያ ዙር ከተመረጡ የክልል ስራ አስፈጻሚ አካላት፣ ከወጣት አደረጃጀቶች ተወካዮች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት መካሄዱንና የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በሐረሪ ክልል ምክር ቤቱ እንዲቋቋም መደረጉ በተለይ የክልሉን ወጣት ድምጽ ለመስማት፣ ፍትሃዊ አሰራሮችንና ተጠቃሚነትን ለማስፈን፣ ያላቸው እምቅ አቅም፣ እውቀትና ክህሎት ከወጣቶች ባለፈ ለክልሉና ለሀገር እድገት የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት የእንኳን ደስ አላችሁ በማለት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ምክር ቤቱ ዓላማውን እንዲያሳካ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ መንግስት እና ባለድርሻ አካላትም ምክር ቤቱን ለማጠናከር በትኩረት እንዲሰሩ በአጽዕኖት አሳስበዋል።

ለተመረጡ ስራ አስፈጻሚ አካላት መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል፤ ኃላፊነታቸውንም በሚገባ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዕለቱ ምክር ቤቱን በቀጣይ አመታት የሚመሩ ስራ አስፈጻሚ አካላት ምርጫ የተካሄደ ሲሆን የክልሉ የወጣቶች ምክር ቤትፕሬዝዳንት ወጣት ባህሩ አብዲ ሆኖ ተመርጧል።

እንደአገር የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ለወጣቶች ድምፅ በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ፣ መጋቢት 24/2015 ዓ.ም መመስረቱ የሚታወስ ሲሆን የዛሬውን መድረክ አስመልክቶ  የወጣቶች ምክር ቤት አላማና ተልዕኮ እንዲሁም የምሥረታ ሂደትን የተመላከቱ ዝርዝር ጉዳዮች ቀርበው የጋራ ግንዛቤ ተወስዷል።

Please follow and like us: