“መንግስት የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ደሃና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የመደጋገፍ ተግባር መጠናከር አለበት” – ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኢርጎጌ ተስፋዬ

መንግስት የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት በተለይም ደሃና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኢርጎጌ ተስፋዬ ገልፀዋል።

ሆኖም መንግስት የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ደሃና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የመደጋገፍ ተግባር መጠናከር አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ግለሰቦችና በጎ አድራጎት ድርጅቶች እጅግ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከኢቢ አካዳሚ ጋር በመተባበር የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የተዘጋጀው ማዕድ የማጋራትና የድጋፍ መርሃ ግብር ለዚህ ዓብይ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ክብርት ሚኒስትሯ ኢቢ አካዳሚ ላደረገው የበጎ አድራጎት ስራና ድጋፍ በሚኒስቴር መ/ቤቱ እና በተጠቃሚ ወገኖች ስም አመስግነዋል።

በቀጣይም ይህንኑ ልምድ ለሌሎች ማጋራት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ ትምህርት ቤቶች ከእውቀት መገብየት ጎን ለጎን ታዳጊዎች በጎነትን እንዲወርሱ እና ለሌሎችም አርአያ እንዲሆኑ ለማስተማር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት በበጎ ፈቃድ ተግባር በሰፊው ቢሳተፉና ካላቸው ላይ ቢያካፍሉ ችግሮቻችንን በጋራ መቅረፍ እንችላለን ብለዋል፡፡

የሚኒስቴር መ/ቤቱ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁርያ አሊ በበኩላቸው የዜጎቻችንን ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ትብብርና መረዳዳት ዋነኛው መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ የኢቢ አካዳሚ በዓሉን ከወገኖቻችን ጋር ለማክበርና ፍቅራችንን ለመግለጽ እንዲያስችል ከሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ጋር በመተባበር ለበጎ ሰራ እየተባበረ እና ማህበራዊ ኃላፊነቱንም እየተወጣ በመሆኑ የሚያስመሰግን ተግባር ነው ብለዋል።

የኢቢ አካዳሚ ት/ቤት አመራሮች በበኩላቸው ማዕድ የማጋራት መርሀ ግብር ላለፉት 13 ዓመታት ከት/ቤቱ ክበባት መምህራንና የት/ቤቱ ማህበረሰብ በማሰባሰብ ሲያዘጋጁ መቆየታቸው ገልፀዋል።

Please follow and like us: