የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወጣቶች ምክር ቤት ተመሰረተ ::

በምስረታ መርሀ ግብሩ ላይ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ወጣቶች ካላቸው እምቅ አቅም፣ እውቀትና ክህሎት አንፃር ራሳቸውን ከመለወጥ ባለፈ ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት የወጣቶችን ችግሮች ለመፍታት፣ መብታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ሚኒስትር ድኤታዋ አክለውም ህገ- መንግስቱንና ፖሊሲውን መሰረት በማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ የወጣት አደረጃጀቶች ተቋቁመው የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ሆኖም እንደሀገር በመንግስትና በወጣቶች መካከል ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል፥ በወጣቶች የሚመራና ከመንግስት ጋር በመመካከር የሚሰራ እውነተኛ የወጣቶች ድምፅ የሚሆን ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በንግግራቸው እንደገለፁት
በምክንያታዊነትና በሀሳብ የሚያምን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስጠብቅ ወጣት በማነፅ በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

መንግስት የወጣቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በገጠርም ሆነ በከተማ በስራ ዕድል ፈጠራ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም በወጣቱም በኩል ከስራ ፈላጊነት ይልቅ የስራ ፈጠራ ሀሳቦች ጎልተው መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ገነት መኩሪያ በበኩላቸው በክልሉ የወጣቶች ምክር ቤት እንዲቋቋም መደረጉም በተለይም የክልሉን ወጣቶች ድምፅ ለመስማት፥ ፍትሃዊ አሰራሮችን ለመዘርጋትና ተጠቃሚነትን ለማስፈን በአጠቃላይም በወጣቶች ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማሳካት የላቀ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።

ዛሬ በተደረገዉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወጣቶች ምክር ቤት ምስረታ 13 ሥራ አስፈጻሚና 42 የምክር ቤት አባላት ተመርጠዋል።

ምክር ቤቱ ወጣት ይስሃቅ ንጉሴን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አድርጎ መርጧል።

 

በመድረኩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚዎች፥ የሃይማኖት ተወካዮች፥ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች፥ የፌደራል የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች ከየመዋቅሩ የተውጣጡ የወጣት አደረጃጀት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ ስለእናት እስከዳር

Please follow and like us: