የህጻናት ጉዳይ አያያዝ ስርዓት አተገባበርና ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተካሄደ

የህጻናት ጉዳይ አያያዝ ስርዓት አተገባበርና በባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

 

በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ በሀገራችን በተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት ህጻናት ለከፋ ችግር ተጋላጭ ስለሚሆኑ ጉዳያቸው ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ የህጻናት ጉዳይ አያያዝ ስርዓት ማዕቀፍ በመቅረጽ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል።

 

ሆኖም በተለይ በመረጃ አያያዝና ልውውጥ ረገድ ወሱንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

ለዚህም በማኑዋል መልክ ያለውን አሰራር ወደ ዘመናዊ ስርዓት መለወጥ ያስፈልጋል ያሉት አማካሪዋ፥ እንደሀገር ወጥና ለአጠቃቀም ምቹ የሆነ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የመረጃ ቋት መዘጋጀቱንና በቅርቡ ወደ ቋቱ መረጃ የማስገባት ስራ ለማስጀመር ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

የመድረኩ ዋና ዓላማም እስካሁን በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት፣ ባጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ መረጃ ከመለዋወጥ ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ የህጻናት ጉዳይ አያያዝ ስርዓት አተገባበርና በባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለምክክር ያለመ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በዕለቱ ብሔራዊ የህጻናት ጉዳይ አያያዝ ስርዓት ማዕቀፍ፣ በአማራጭ የህጻናት የድጋፍና ክብካቤ መመሪያ፣ በህጻናት ጥበቃ ዙሪያ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን የክልሎችና ሴክተር ተቋማት አፈጻጸም ሪፖርትም ተደምጧል።

 

በቀረቡ ሰነዶች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን መፍትሄ ይሻሉ ተብለው ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጉዳዮች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና የቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በምክክር መድረኩ ለቅብብሎሽ ስርዓቱ እንዲያግዝ ከፌዴራል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ከክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

Please follow and like us: