የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች ውጤት እያሳዩ ነው

የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማሳየታቸውን የኢትዮጵያ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር ገለጸ።

የስጋ ደዌ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ በሐረር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።የኢትዮጵያ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ከፍያለው በቀለ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በስጋ ደዌ ተጠቂዎች ላይ ቀደም ሲል ይደርስ የነበረው መገለል ሙሉ ለሙሉ ባይቀረፍም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ለውጥ አለው።

የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ከጥገኝነት ተላቀው የራሳቸውን ህይወት መምራት ችለው ማየታቸውን ገልጸው፤ በዚህም በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መታየቱን አክለዋል።

የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማደግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጨመር እንደ አንድ ምክንያት አንስተው፤ መንግስት ትኩረት የሰጠበት ሁኔታም ለውጤቱ መሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።

የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲሁም የሚደርስባቸውን መድሎና መገለል ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ አሁንም በርካታ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።ማህበሩ ተልዕኮውን ለማሳካት ከመንግስት፣ ከባለድርሻ አካላትና ከሌሎች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ከፍያለው፤ ይህ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ማህበረሰቡ ለስጋ ደዌ ተጠቂዎች ሁሉን አቀፍ ምላሽ መስጠት ይገባዋል ያሉት ደግሞ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሳልፈው አመዲን ናቸው።የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ስራዎችም መጠናከር ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር በበኩላቸው የስጋ ደዌ ተጠቂዎች መብትና ጥቅም የሚጠናከርበትና በሽታውን ለማጥፋት በጋራ የምንመክርበት በዓል ነው ብለዋል። 0ይህም ህብረተሰቡ ለስጋ ደዌ ህሙማን የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር ለማጠናከር እንደሚያግዝ አመልክተዋል። በክልሉ በሽታው የሚያስከትለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል የህክምና አሰጣጥ ስርዓቱ እንዲጠናከር መደረጉን ጠቁመው በተከናወነው ስራም ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።ቀኑን ምክንያት በማድረግም በትናንትናው ዕለት የእግር ጉዞ በከተማው ተካሂዷል።

ዛሬ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎእ፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የስጋ ደዌ ታማሚ ዜጎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የዘንድሮ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቀን በዓል እየተከበረ ያለው “የስጋ ደዌ በሽታን አንዘንጋው” በሚል መሪ ሃሳብ ነው ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Please follow and like us: