“ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ማህበረሰቡን ጨምሮ እያንዳንዱ ዜጋ ሊረባረብ ይገባል” – ክብርት ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

የኦሮሚያ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል።

በመድረኩ የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚካሄድባቸው ክልሎች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የኦሮሚያ ክልል መሆኑን ጠቅሰው፤ በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ለአካላዊ፣ ለስነልቦናዊ፣ ለኢ- ሰብዓዊ ድርጊቶች አልፎም ለህልፈተ ህይወት እየተዳረጉ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

መንግስት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን የመከላከል፣ ተመላሽ ዜጎች ተገቢውን የስነ-ልቦና እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት እንዲሁም የተመላሽ ዜጎችን መረጃ የማደራጀት እና የማሰራጨት ስራ በቅንጅት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ድርጊቱን ለመከላከል ማህበረሰቡን ጨምሮ እያንዳንዱ ዜጋ ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አሰተባባሪ አብዱል ሀኪም ሙሉ በበኩላቸው፤ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በሚያከናውኑ አዘዋዋሪዎች ላይ ክልሉ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል።አያይዘውም ከስደት ተመላሽ ዜጎችን ለማቋቋም ክልሉ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዜጎች ላይ የሚደርሰው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከማህበረሰብ ባለፈ ለሀገር እድገት ጠንቅ በመሆኑ፤ ይህንን ለመከላከል ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት በክልሉ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑም ተጠቁሟል።

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ መንግስት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ባሻገር፤ በተጠናከረ የማህበረሰብ ተሳትፎ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከል ያስፈልጋልም ተብሏል።

በመድረኩ የፌዴራል እና የክልል የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

 

ዘጋቢ ስለእናት እስከዳር

Please follow and like us: