“የሴቶችን አቅም ለማሳደግና ለማብቃት ሁሉም በትብብርና በቅንጅት መንፈስ ሊሰራ ይገባል” – ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2016 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ምዝገባ መክፈቻ እና 21ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይሚንስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ተገቢውን ስፍራ እንዲያገኙ፣ ድምጻቸው እንዲሰማ፣ መብታቸው እንዲከበርና በስፖርቱ ከተጎናጸፉት ስኬት ባሻገር በሌሎችም መስኮች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ሰፊ ትግል ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሴቶች ያሉባቸው ችግሮች ከተቀረፉላቸው፣ ጥረታቸውን ከጎን ሆኖ ማበረታታት ከተቻለ፣ በየመስኩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸውና ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ተጠቃሚ ከተደረጉ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከመለወጥ ባለፈ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚበረክቱ ገልጸዋል።

ሴቶችን ለማብቃትና ለመደገፍ በመንግስት በኩል በተወሰዱና እየተወሰዱ ባሉ ጠንካራ እርምጃዎች ሴቶች በየመስኩ ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ጠቁመዋል።

እንደሀገር የተጀመረው ለውጥ እንዲፋጠን ሴቶች ድርሻቸው የላቀ በመሆኑ የሴቶችን አቅም ለማሳደግና ለማብቃት ሁሉም በትብብርና በቅንጅት መንፈስ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሴቶችም “በእንችላለን መንፈስ” በስፖርቱም ሆነ በሌሎች ዘርፍ በንቃት መሳተፍና አቅማቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል።

 

 

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እና አጋሮቹ በሴቶች ዙሪያ ለሚከናወኑ ተግባራት እያደረጉት ላለው ድጋፍ ሚኒስትሯ አመስግነዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዳግማዊት አማረ ባለፉት 21 ዓመታት የሴቶችን ስኬት ለማክበር፣ ሴቶችን ለማብቃትና ማህበራዊ መልዕክቶች ለማስተላለፍ፣ እርስ በእርስ ልምድ ለመለዋወጥ እንዲሁም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሴቶችንና በጎ አድራጎት ተቋማትን ለመደገፍ ተችሏል ብለዋል።

የውድድሩ ተሳታፊዎች ሴቶች ቁጥር ከ4ሺህ 500 አሁን ላይ 16ሺህ መድረሱም ትልቅ ስኬት መሆኑ በመድረኩ ጠቁመዋል።

የሩጫ ውድድሩ ከዘንድሮ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ጋር በማስተሳሰር “የሴቶችን አቅም እንደግፍ፣ ለውጥን እናፋጥን በሚል መሪ ቃል መጋቢት ላይ እንደሚካሄድ ተመልክቷል።

Please follow and like us: