መንግስት ለሁሉም አካላት የሰላም ጥሪ በማቅረብ ከለውጡ ጀምሮ እስካሁንም ለዘላቂ ሰላም ብዙ ጥረት እያደረገ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

መንግስት ለሁሉም አካላት የሰላም ጥሪ በማቅረብ ከለውጡ ጀምሮ እስካሁንም ለዘላቂ ሰላም ብዙ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ሲሆን ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አንዱ ሲሆን በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ መንግስት ምን እየሰራ ነው ሲሉ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የጸጥታ ችግሩ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ማእከል ያደረገ ሳይሆን ለግል ጥቅም ሲሉ በሚንቀሳቀሱ አካላት የሚፈጠር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የጥፋት አካላት አበክረው የሚፈልጉት እና የሚሰሩት ለሰላም ሳይሆን ለግጭትና ጦርነት መሆኑን ገልጸዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ጀምሮ መንግስት ለሁሉም አካላት የሰላም ጥሪ በማቅረብ እስካሁንም ለዘላቂ ሰላም ብዙ ጥረት ያደረገ ቢሆንም የተቀበሉ እንዳሉ ሁሉ በጥፋት የቀጠሉ እንዳሉ አንስተዋል።

በአማራና ትግራይ ክልል መካከል የሚነሳውን የወሰን ጥያቄ ዘላቂ ሰላም በሚያመጣ መልኩ በውይይትና ምክክር ምላሽ ለመስጠት የታቀደ ቢሆንም በግጭትና ጦርነት ምክንያት እስካሁን የታሰበውን ማሳካት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

በመሆኑም በኦሮሚያም ይሁን በአማራ ክልል ትጥቅ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች የጥፋት መንገድን ትተው የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ጠይቀው መንግስትም ለሰላም አማራጭ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

Please follow and like us: