የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM)ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነ የፍልሰት አስተዳደር እንዲኖራት እገዛ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM) ካውንስል ሰብሳቢ፣ በጄኔቫ የጀርመን አምባሳደርና የተባበሩት መንግስታት ቋሚ መልክተኛ እና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች በጄኔቫ ወኪል ከሆኑት አምባሳደር ካትሪና ስታሽ ጋር ተወያይቷል።

በዉይይቱ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከል፣ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል ፡፡መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በኢትዮጵያና በአጠቃላይ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ እያስከተለ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ለመቀነስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በስፋት እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ተመላሽ ዜጎች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው መልሰው ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለይም ከአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ጋር በቅንጅትና በትብብር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ዙሪያ ለአምባሳደር ካትሪናንና ለልዑካን ቡድናቸው ዝርዝር ገለጻ አድርገዋል።

 

አምባሳደር ካትሪና በበኩላቸው ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከልና የፍልሰት ተጎጂዎችን በመደገፍና መልሶ በማቋቋም እያደረገች ያለችውን ጥረት አድነቀው፣ በቀጣይ ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነ የፍልሰት አስተዳደር እንዲኖራት ለማድረግና የሴቶችን አቅም ለመገንባት እገዛ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ ስለእናት እስከዳር

Please follow and like us: