የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሠጣጥን ለማሻሻልና የባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ያለመ ስልጠና ተሰጠ

በአዲስ መልክ በተደራጁና በነባር ክልል ስር የሚገኙ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሠጣጥ ለማሳደግና የባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ያለመ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ይገኛል።

በመድረኩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ህጻናት ቀልጣፋና ሁሉን አቀፍ የሆነ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን አሰራር ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግና የማስፈጸም አቅምን ለማጎልበት በየጊዜው ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ተገልጿል።

ስልጠናው በዋነኝነት የስነ አዕምሮ፣ የማህበረሰብ ጤና እና የስነልቦና ድጋፍ አሰጣጥ እንዲሁም ጭንቀትን ማርገብና የአዕምሮ ደህንነት ብሎም የህጻናት ጉዳይ አያያዝ እና አስተዳደር ላይ ያተኮረ ሲሆን በዘርፉ የሚስተዋለውን የማስፈጸም አቅም ውስንነት ለመሙላት እንደሚያግዝ ተጠቁመዋል።

ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ላጋጠማቸው ሴቶችና ህፃናት ምላሽ የሚሰጡ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ለማጠናከር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ተብሏል።

ጥቃትን አስቀድሞ ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ለተጎጂ ሴቶችና ህጻናት ተገቢውን የምክር፣ የማህበረ – ስነልቦና ድጋፍ በመስጠት ረገድ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በቅንጅት እንዲሰሩና የቡኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

ሰልጣኞች ከንድፈ ሃሳብ በተጨማሪ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ጉብኝትና ተግባር ተኮር ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል።

በስልጠና መርሀ ግብሩ ከጋምቤላ፣ ከደቡብ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከሲዳማ ክልል የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

Please follow and like us: