ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ቀጣናዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ተናገሩ።

ህገ ወጥ ስደተኝነትን ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ “ቀጠናዊ የስደተኞች ምላሽ እቅድ ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን እና ደቡብ አፍሪካ 2024” ይፋ ተደርጓል። በመድረኩ በኦንላይን የተሳተፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በስራ ማጣት እና በሌሎችም ገፊ ክንያቶች ህገ ወጥ የሰዎች ፍልሰት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ዜጎችን በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ በመጣል ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ለአካላዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች እየዳረጋቸው ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ የሰዎችን ህገወጥ ፍልሰት ለመከላከል ቀጠናዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። ቀጠናዊ የስደተኞች ምላሽ ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን እና ደቡብ አፍሪካ 2024 እቅድ በተለያዩ ምክንያቶች መደበኛ ላልሆነ ፍልሰት የሚዳረጉ ዜጎችን ለመታደግ እና ህገ ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል የሚያስችል መመሪያ ነው። በመድረኩ ላይ ከመስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ ከአለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት እና ከሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ ስለእናት እስክንድር

Please follow and like us: