“የሴቶች መብት ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እስኪከበር ድረስ ሁላችንም በጋራ መተባበርና መስራት ይኖርብናል” – ክብርት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አለም አቀፉ የሴቶች ቀን ወይንም ማርች 8 በአድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሀ ግብሮች በድምቀት ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንትና የዕለቱ የክብር እንግዳ ክብርት ሣህለወርቅ ዘውዴ ሴቶችን ለማብቃት ትምህርት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ሴት የዩኒቪርሲቲ ተማሪዎች ሜንቶርሺፕ ፕሮግራም ማስጀመራቸውንና ለ1500 ያህል ሴቶች ዕድል መሠጠቱን ተናግረዋል። ይህን ብሔራዊ ፕሮግራም ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በሌላ በኩል መሠረት የሆኑትን የገጠር ሴቶችንም ለማስተማርና ለማብቃት ትኩረት መሠጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ሁሉንም ዓይነት የሴቶች ጥቃት መከላከልና ማስቆም ያስፈልጋል፤ በተለይም ደግሞ በሴቶች ማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከሁሉ የከፋ በመሆኑ መቆርቆና ነቅቶ መታገል ይገባል ብለዋል። የሴቶች መብት ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እስኪከበር ድረስ ሁላችንም በጋራ መተባበርና መስራት ይኖርብናል ሲሉ ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አሳስበዋል።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለቀደምት ማርች 8 ምክንያት በማድረግ ከወትሮ በተለየ በየደረጃው በተካሄዱ የንቅናቄ ስራዎች የተለያዩ ሰው ተኮር ልማታዊና ውጤታማ ተግባራት መፈጸሙንና ለችግር ለተጋለጡ ሴቶችና ህጻናት ሀብት በማሰባሰብ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል። ለአብነትም በንቅናቄው አቅመ ደካማ ለሆኑ ሴቶችና ህፃናት እንዲሁም በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ለኢኮኖሚ ችግር ለተጋለጡ ዜጎች ከ94 ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የአልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በቁጠባና ብድር በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በየደረጃው የነበረውን የቅንጅት ችግር በመፍታት 1,799,412 ሴቶች ቁጠባ ያካሄዱ ሲሆን በዚህም 685,177,860.00 መቆጠብ ችለዋል፡፡  የተጀመሩ ተግባራት ወደፊትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። በዓሉ በዋናነት የሚከበረው በሴቶች ላይ ይደርሰ የነበረውን ጭቆና ለማውገዝ፣ ሴቶች በአደባባይ ቆመው ሀሳባቸውን እንዲገልጹ ብቻ ሳይሆን እድል ካገኙ የትኛውንም የሀገራችን እድገትና ለውጥ ሊያፋጥኑ በሚችሉ ዘርፎች ከወንድ አጋሮቻችን ጋር በህብረትና በእኩል በመሠለፍ በውጤትና በስነ ምግባር የታጀበ ተግባር መፈጸም እንደሚችሉ ያረጋገጡበትን ሂደት ለማውሳት፣ ለቀደምት ሴት ጀግኖች ትልቅ ክብርና ምስጋና ለማቅረብ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በበኩላቸው አስተዳደሩ የሴቶች የተሃድሶና የልህቀት ማዕከል ማስገንባቱን ገልጸዋል። ማዕከሉ በየአመቱ 10ሺህ ለሚሆኑና በተለይም ደግሞ ለተሰማሩ ሴቶች የመጠለያና የስልጠና አገልግሎት በመስጠት በሙያቸው የራሳቸውን ስራ መስራት እንዲችሉ የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

Please follow and like us: