የቤተሰብ የምክር አገልግሎት፤ ምንነት እና አተገባበር! – (ክፍል ፩)

ቤተሰብ ጥበቃ ይፈልጋል፤ ጥበቃውም እውን የሚሆነው በራሱ በቤተሰብ፣ በህብረተሰቡ እና በመንግስት ነው፡፡ ይህም በተለያዩ ህጎች ላይ ተመላክቷል፡፡ ቤተሰብ የሰው ልጅ/ ትውልድ የሚገነባበት፣ የህብረተሰብ መሰረታዊ ተፈጥሯዊ መነሻና ትልቅ የማህበራዊ ተቋም በመሆኑ ችግር ላይ ከወደቀ ጉዳቱ የህብረተሰብ ብሎም የሀገር ነው፡፡
ይሁንና የቤተሰብ ግንኙነት ቋሚ እና ዘወትራዊ በመሆኑ ከግጭት እና አለመግባባቶች ነፃ ሊሆን አይችልም፡፡ በውስጣዊ ግጭት ምክንያት ደግሞ የቤተሰብ መሰረት እንዳይናድ የችግሩ ምንጭ በአግባቡ ተለይቶ መታወቅና በጥልቅ ውይይት እና ንግግር በፍጥነት መታከም ይኖርበታል፡፡ ሂደቱም የተጠና እና የታወቁ ቅደም ተከተሎች ያሉት በመሆኑ ያን መከተልና መተግበር ይበልጥ ውጤታማ ያደርጋል፡፡
የቤተሰብ የምክር አገልግሎት ምንነት በቀላል አገላለጽ በቤተሰብ አባላት መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት እና ተገቢውን መፍትሔ ለማምጣት የሚከናወን አገልግሎት እና የተፈጠረው ችግር በውይይት እና በንግግር እንዲፈታ የሚደረግበት ሂደት ነው፡፡ ጠቀሜታውም በቤተሰብ አባላት መካከል የውይይት/የንግግር ባህል እንዲሻሻል፣ ግጭትና ውጥረት እንዲቀንስ፣ የባህሪ መሻሻል እንዲመጣ፣ ጤናማና ዘላቂ ግንኙነት እንዲፈጠር፣ የቤት ውስጥ ችግሮችን የመቋቋም እና ፈጥኖ የመመለስ/የማገገም እና ቀና የመሆን ፍላጎትና ክህሎት እንዲያድግ ይረዳል፡፡ የምክር አገልግሎቱ ተግባቦትን (ኮምዩኒኬሽንን) በማሻሻል እና ግጭቶችን በማርገብ፣ የቤተሰብ አባላትን ግንኙነት በቋሚነት ማሻሻል ላይ ያተኩራል፡፡ ስለሆነም ለቤተሰብ እና ለአባላቱ ደረጃውን የጠበቀ ውጤታማ የቤተሰብ የምክር አገልግሎት ሊኖር ይገባል፡፡ አገልግሎቱም ተጠያቂነት እና ህጋዊ መሰረት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡
የቤተሰብ የምክር አገልግሎት አቅራቢዎች ሚና
አማካሪዎች ለሥራው እጅግ ብቁ፣ ልምድና ፈቃድ ያላቸው እንዲሁም በብርቱ ጥንቃቄ የሚሰሩ መሆን አለባቸው፡፡
በምክር አገልግሎቱ ሂደት እነማን ሊሳተፉ ይችላሉ?
እንደችግሩ ስፋት እና ቀጥታ ጉዳዩ እንደሚመለከታቸው የቤተሰብ አባላት ሁሉም በምክር አገልግሎቱ በባለቤትነት መሳተፍ ይችላሉ፡፡
የቤተሰብ የምክር አገልግሎት ግቦች
1. ለማስተማር እና እርስበርስ ለመማማር፣
2. የቤተሰብ አባላት እንዲመካከሩ/እንዲወያዩ ለማስቻል፣
3. የቤተሰብን ደህንነት ለማስጠበቅ፣
በአጠቃላይ፡- ችግሮችን በፍጥነት መፍታት፣ ይቅርታ ማድረግ እና ይቅርታ መጠየቅን የማስለመድ እና ሠላማዊ የቤተሰብ ግንኙነቶችን የማጠናከር ውጤት አለው፡፡
በክፍል ፪ ከቤተሰብ የምክር አገልግሎት ጋር የተያያዙ ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን የምናጋራችሁ ይሆናል።
በዋሲሁን ቢምረው
Please follow and like us: