የቤተሰብ ደህንነት መጠበቅ ለአረጋውያን የቤት ለቤት ድጋፍ እና እንክብካቤ መጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ::

“ከአረጋውያን እንማር፤ እንደ ቤተሰብ እንደጋገፍ” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ አቶ ጌታቸው በዳኔ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትር አማካሪ፥ በተለያዩ የጥናት ውጤቶች እንደተመለከተው አረጋዊያን እጅግ ደሃ እና ተጋላጭ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እየተስፋፋ የመጣው የውድድርና ተናጥላዊ የአኗኗር ዘይቤ በህብረተሰቡ ዘንድ የአረጋውያን መሠረታዊ መብቶች እንዲዘነጉ አድርጓል ብለዋል፡፡ በአረጋውያን ላይ የሚደርሱ ችግሮች ዘርፈ ብዙ መሆናቸውንና በአንዳንድ አከባቢዎች ከወንዶች ይልቅ ሴት አረጋዊያን ለከፋ ለችግር የሚጋለጡበት ሁኔታ መኖሩንም ገልጸዋል።

መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማጣት ብቻም ሳይሆን ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊዳረጉ እንደሚችልም አንስተዋል፡፡ ይህም አረጋዊያን ደህንነታቸውን እንዳይጠበቅና መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን እንዳያሟሉ እንዲሁም ያላቸውንም ተፈጥሯዊ ጸጋና የህይወት ልምድ በአግባቡ እንዳይጠቀሙ እና ለትውልዱ እንዳያስተላልፉ ያግዳቸዋል ብለዋል፡፡

ስለሆነም አረጋዊያን የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ እና ቢያንስ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያስችል የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው እና የቤት ለቤት ድጋፍ እና እክብካቤ አገልግሎቶች እንዲሟሉላቸው ቢመቻች ይበልጥ ተመራጭ እንደሚሆን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እና የህግ ማዕቀፎች ያበረታታሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ስኬት ደግሞ የቤተሰብ ሚና እና አቅም ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል ያሉት ኃላፊው፥ የአረጋውያን የቤት ለቤት ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲጠናከር አስቀድሞ የቤተሰብ ደህንነት ሊጠበቅ እንደሚገባ አያይዘው ገልጸዋል። የቤተሰብ ደህንነት አደጋ ላይ በወደቀ ቁጥር አባላቱ ከመበተን ባለፈ አረጋውያንን ጨምሮ በቤት ውስጥ ያሉ አባላት ለበለጠ ፈተና እና የህይወት ተግዳሮቶች ይጋለጣሉ ብለዋል፡፡

በመሆኑም በአረጋውያን እና ቤተሰብ ዙሪያ የሚሰሩ  ባለድርሻና አጋር አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡና የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችንም ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

Please follow and like us: