“የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስወገድ የሚደረገው ውጤታማ እንዲሆን የተቋቋመውን ጥምረት ማጠናከርና መደገፍ ይገባል” – አቶ ጌታቸው በዳኔ

የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስወገድ የተቋቋመውን ጥምረት ለማጠናከርና ሚናውን ለማጎልበት ያለመ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትር አማካሪ አቶ ጌታቸው በዳኔ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ ሴቶችንና ታዳጊ ህጻናትን ውስብስብ ለሆነ አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ስነልቦናዊና የጤና ችግር የሚዳርግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሆኑ ድርጊቱን ለመከላከልና ለማስቆም የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱን ለማስቆም ሀገራችን ኢትዮጵያ ቃል ኪዳን መግባቷን ብሎም ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን እና ብሔራዊ ጥምረት በየደረጃው ተቋቁሞ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገሩን ተናግረዋል።ባለድርሻና አጋር አካላትን በማስተባበር ሰፋፊ ስራ እየተሰራና አበረታች ውጤት እየተገኘ ቢሆንም አሁንም ድርጊቱ የሚፈጸምበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል። እንደሀገር ድርጊቱን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

በተለይ በፌዴራልና በክልል ደረጃ የተቋቋመውን ጥምረት ማጠናከርና መደገፍ ሀገራችን ለገባችው ቃል ኪዳን ተፈጻሚነት ፋይዳው የላቀ በመሆኑ የጥምረቱን የማስፈጸም አቅሙን ለማጎልበት እንዲያስችል የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በመድረኩ ጥምረቶችን ከማጠናከር አንፃር በየደረጃው እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የተገመገሙ ሲሆን የሴት ልጅ ግርዛት እና የህጻናት ጋብቻ ለማስወገድ እየተተገበረ ባለው ፍኖተ ካርታ አፈፃፀም ዘሪያ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ውጤትም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች መብት ስርጸት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙሉአለም ጌታ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። ከጥናት ግኝቱ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎችም በሚኒስቴር መ/ቤቱ የህፃናት መብትና ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ እንዲሁም በሴቶችና ህፃናት ዘርፍ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ሰለሞን አስፋው አማካኝነት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል። በተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት የተደረሰ ሲሆን የብሔራዊ ጥምረቱ የቀጣይ እቅድ ላይም በተመሳሳይ ውይይት ተካሂዶ እንዲፀድቅ ተደርጓል።

Please follow and like us: