“የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ህጻናት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የበጎ አድራጎት ተቋማትን ለማጠናከርና ሌሎችንም ለማስፋፋት ሁላችንም መርዳት አለብን” – የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አለም አቀፉ የዳውን ሲንድረም ቀን “ፍረጃ ይቁም! እኛ ሰዎች ነን፤ እንደሰው ያዙን” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሀ ግብሮች በድምቀት ተከብሯል።

በዚሁ ጊዜ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዳሉት የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ ህልማቸውን ማሳካት ይችላሉ፡፡ “የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት የፈጣሪ ቁጣ አይደለም” ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን መደገፍና ለስኬት እንዲበቁ ማገዝ ይገባል ብለዋል፡፡ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸውን ህጻናት ለማገዝ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የበጎ አድራጎት ተቋማትን ለማጠናከርና ሌሎችንም ለማስፋፋት ሁላችንም መርዳት አለብን” ብለዋል። በተሳሳተ ግንዛቤ ቤት ተዘግቶባቸው የዛሬውን የተስፋ ብርሃን ሳያዩ የቀሩ በርካታ ህጻናት መኖራቸውን አንስተዋል።

ነጋቸው ብሩህ ህልማቸው እውን እንዳሚሆን በማመን እንደዲቦራ ፋውንዴሽን፣ ፍቅር የአእምሮ እድገት ውስንነት ማህበር ያሉ የበጎ አድራጎት ተቋማት እያደረጉ ያለው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበኩሉን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ዲቦራ ፋውንዴሽን ለህጻናቱ እና ለቤተሰቦቻቸው የተስፋ ብርሃን ሆኗል ያሉት ሚኒስትሯ ለህጻናቱ ዕድል በመስጠት በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት አካላትን በሙሉ አመስግነዋል።የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፤ በየአመቱ ከ3000-3500 ህጻናት ከዳውን ሲንደረም ጋር ይወለዳሉ ብለዋል።ጤና ሚኒስቴር በቀጣይ በዳውን ሲንድረም ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤና የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ እንዲሁም በዘርፉ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደረሽነት ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።

 

የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራችና ፕሬዝደንት አቶ አባዱላ ገመዳ በኩላቸው ፋውንዴሽኑ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆች የክህሎት ስልጠና በመስጠት ራሳቸውንና ቤተሳባቸውን እንዲያግዙ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች እንደማንኛውም ሰው ሳይንቲስት፣ ኢንጂነሮችና አገር መሪዎች መሆን ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ስለችግሩ ያለውን ግንዛቤ በማስተካከል ድጋፍና እንክብካቤ ሊያደርግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉን ምክክያት በማድረግ ጉዞ ከዲቦራ ጋር በሚል የእግር ጉዞ የተካሄደ ሲሆን መልካም ለሰሩ አካላትም የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከዳውን ሲንድረም ጋር የሚኖሩ ታዳጊ ህጻናት፣ ወጣቶችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ሌሎች የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

Please follow and like us: