“ሀገር ከሚያጋጥማት ችግር የሚያወጣ ትውልድ ለመፍጠር ህፃናት ላይ መስራት ያስፈልጋል” – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ሀገር ከሚያጋጥማት ፈተና የሚያወጣ ትውልድ ለመፍጠር ህፃናት ላይ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

መቅደስ የልጆች አድማስ የበጎ አድራጎት ድርጅትን በዛሬው ዕለት በይፋ ስራ የማስጀመሪያ መርሐግብር ተከናውኗል። የማዕከሉን የስራ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ በብይነ መረብ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ሀገር ከሚያጋጥማትና እያጋጠማት ካለው ችግር የሚያወጣ ትውልድ ለመፍጠር ህፃናት ላይ መስራት ያስፈልጋል።

በጦርነት፣ በበሽታና በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን በመርዳት ሀገር ካለችበት ችግር ማውጣት ያስፈልጋል ብለዋል። መቅደስ ልጆች አድማስ በጎ አድራጎት ድርጅት በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን የመረዳዳት ባህልን ለማጠናከር ተምሳሌት ነው ሲሉ ተናግረዋል። መቅደስ ያለመችውና እያደረገች ያለው የበጎ አድራጎት ስራ በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን እንድናስብ፣ እንድንደግፍ የሚያደረግ የተቀደሰ ስራ ነውም ብለዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ህፃናትን በመልካም ምግባር አንጾ ማሳደግ የሀገርን ዕድገት እውን ለማድረግ ይጠቅማል። የህፃናትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግራቸውን በመቅረፍ ተንከባክቦ ማሳደግ ለሀገር እድገት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል። መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን መብትና ማህበራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የህጻናት ድጋፍና ክብካቤ መመሪያ በስራ ላይ እንዲውል መደረጉን ገልጸዋል።

የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገትና ክብካቤን ለማጠናከር፣ የህጻናት የቀን ማቆያ ለማሰፋፋትና በሌሎችም አማራጭ ፕሮግራሞች ዙሪያ ከአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር እና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን አንስተዋል። የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማትም በበጎ ፈቃድ በመነሳሳት ለችግር የጋለጡ ህጻናትን በመደገፍ የመንግስትን ጥረት እያገዙ ይገኛል፤ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ማዕከሉ ለችግር የተጋለጡ ህፃናትን በማገዝ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት ትልቅ አስተዋፆ አለው ያሉት ሚኒስትሯ የህፃናትን ደህንነት ለመጠበቅና ለመደገፍ የሚያከናውነው በጎ ተግባር እንዲሳካ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። መቅደስ የልጆች አድማስ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ መቅደስ ጸጋዬ ለማዕከሉ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ እቅርበዋል።

 

Please follow and like us: