“የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ አቅምን ባገናዘበ እና ንፅህናውን በጠበቀ መልኩ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት መስራት ይገባል”     – (ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ አሞድ)

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ተደራሽነትና አቅርቦት ሂደትን የሚመራ ስትሪንግ ኮሚቴ ለማቋቋምና ቀጣይ ተግባራት ላይ ለመወያየት ያለመ መድረክ አዘጋጅቷል።

በመድረኩ ላይ የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ አሞድ የወር አበባ ሴቶች የተፈጥሯዊ ጸጋና ትውልድን ለማስቀጠል ከፈጣሪ የታደሉት የህይወት ክፍል ቢሆንም በንፅህና መጠበቂያ ምርት ላይ በሚስተዋለው የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ምክንያት ሴቶችና ልጃገረዶች ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ እያዳረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ መንግስት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የቀረጥ ቅናሽ ማድረጉንና ከ2014 ዓ.ም በፊት ከነበረበት ከ30 በመቶ ወደ 10 በመቶ በማውረድ በዝቅተኛ ዋጋ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ሰፊ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ከምርት አቅርቦት፣ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ከኑሮ ውድነት፣ ከጥራትና ከተደራሽነት ጋር በተያያዘ አሁንም ሰፊ ክፍተት መኖሩንና ይህም በተጠቃሚዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል። የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ አቅምን ባገናዘበ እና ንፅህናውን በጠበቀ መልኩ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታዋ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ አሞድ ተናግረዋል። ችግሩን በዘላቂ ለመፍታትም በቀጣይ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታትና መደገፍ፣ አዳዲስ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲገቡ ማስቻል፣ የአጋር ድርጅቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ በስርጭት ሂደት ያሉ ችግሮችን መፍታት እንዲሁም በወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ላይ ያተኮረ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በወር አበባ ላይ ያለውን መገለል ለመስበር እና ጤናማ ልምዶችን ለማሳደግ ለማህበረሰቡ ትምህርት ከመስጠት ጎን ለጎን በትምህርት ቤቶችና በስራ ቦታዎች አካባቢ ለወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ምቹ እንዲሆኑ እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ የፖሊሲ ለውጦች እንዲደረጉ ለማስቻል ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር ፕሮጀክት መቀረጹን ጠቁመው ለተግባራዊነቱ በጋራ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል። የሚቋቋመው ኮሚቴ ከመንግስትና ከግል ሴክተር የሚውጣጣ ሲሆን በእለቱ በአጠቃላይ ማዕቀፉና በፕሮጀክቱ ላይ ለመንግስት ተቋማት አባላት ገለጻ ተደርጓል፤ በቀጣይ ሁሉም የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት ተገናኝተው ፕሮጀክቱን ለማሳካትና የሚታዩ ክፍተቶች ለመፍታት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል ።

 

Please follow and like us: