“እንደሀገር የተቋማት አካቶ ትግበራ ስልት እንዲሳለጥ እና ዜጎችም ከሂደቱ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የአስፈጻሚ አካላት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው”   – ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሴቶችና ህጻናት ልማት ድርጅት ጋር በመተባበር በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ባሉ ለውጦችና ክፍተቶች እንዲሁም መዋቅሩን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔተ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ የሀገራችን ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ሌሎች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ በሁሉም ዘርፍ ትኩረት በመስጠትና አካታች በሆነ መልኩ በመተግበር ረገድ መልካም ጅምሮች ያሉ ቢሆንም አሁንም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን ጠቁመዋል። ለዚህም በሴክተር መ/ቤቶች በአደረጃጀት፣ በመዋቅር፣ በበጀት፣ በሰው ኃይልና ውሳኔ ሰጪነት ረገድ ችግሮች መኖራቸውን በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የክትትል ስራዎች እና የዳሰሳ ጥናቶች ለመገንዘብ ተችሏል ብለዋል፡፡

የአካቶ ትግበራ ጉዳይ በመንግስት በኩል ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጠውም፤ ሂደቱን ለማስፈጸም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መዋቅሮች በየተቋማቱ የተቋቋሙ ቢሆንም በአስፈጻሚ አካላት ዘንድ የቁርጠኝነትና የተጠያቂነት ስርዓት አለመስፈኑ እንቅፋት መፍጠሩን አንስተዋል። እንደሀገር ትግበራው እንዲሳለጥ እና ዜጎችም ከሂደቱ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል መዋቅሩን ማጠናከር ይገባል፤ ለዚህም አስፈጻሚ አካላት ትኩረት እንዲሰጡና በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለአካቶ ትግበራ ውጤታማነት አመቺ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት፣ የተቋማትን አቅም በመገንባት፣ ቅንጅትና ትብብርን በማጠናከር የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን በማድረግ እንዲሁም የአፈጻጸም ደረጃን በመለካት ተጠያቂነትን ለማስፈን በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የስርዓተ ጾታና የአካቶ ትግበራ ጉዳይ የልማት፣ የሰብዓዊ መብት፣ የማህበራዊ ፍትህ እና የእኩልነት ጉዳይ ነው ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ፣ የባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉባቸውን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት፣ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውንም በሂደት ለማረጋገጥ በየዘርፉ የሚደረገው ጥረት በበጀት፣ በመዋቅርና በሌሎችም አግባብ መደገፉን ምክር ቤቱ በቀጣይ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል ብለዋል።

በመድረኩ በስርዓተ ጾታ ምላሽ ሰጪ በጀት አተገባበር፣ በመዋቅር ደረጃ ባሉ ተግዳሮቶች፣ ከአካታችነት አኳያ በአፍሪካና በኢትዮጵያ ባሉ ተሞክሮችና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሰነዶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። ከተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመድረኩ ተሳትፈዋል።

Please follow and like us: