የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ሴቶችና ወጣቶች ለኤች አይ ቪ ያላቸውን ተጋላጭት በመከላከል ዙሪያ ከዪኤን ኤድስ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት አካሂዱ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ሴቶችና ወጣቶች ለኤች አይ ቪ ያላቸውን ተጋላጭት በመከላከል ዙሪያ ከዩኤን ኤድስ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።

ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የዩኤን ኤድስ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍራንሷ ናዴይስሂምዬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በውይይታቸውም፥ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የተቋሙን ኃላፊነት እንዲሁም ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ በሴክተሩ ተደራሽ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች መብት ለማስከበር፣ ማህበራዊ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅና ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በሰፊው አብራርተዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዩኤን ኤድስ ጋር አጋርነትን በማጠናከር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸው በቅንጅት መስራት የሚቻልባቸውንም የትብበር መስኮች በዝርዝር አስረድተዋል።

በተለይም ኤች አይ ቪ በሴቶችና ወጣቶች ላይ የሚያስከትለውን የጤናና ተያያቸዥ ችግሮች ለመቅረፍ ብሎም ስርጭቱን ለመቀነስና ለመግታት የሚያግዙ ተግባራትን በጋራ መስራቱ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣም ያላቸውን እምነት በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል። ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንደሚያደርግ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዩኤን ኤድስ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍራንሷ ናዴይስሂምዬ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል። ዩኤን ኤድስ የነበረውን ግንኙነት ይበልጥ የማጠናከር ዓላማ እንዳለው የገለጹት ዳይሬክተሯ በተለይ ሴቶችና ወጣቶች ለኤች አይ ቪ በሽታ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመከላከልና ሰብዓዊ መብታቸውን ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍና በጋራ ለመስራት እንደሚፈልግ አስታውቀዋል።

ውይይቱን ተከትሎም ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድን እንዲቋቋም እንዲሀም በአጭርና በረጅም ጊዜ ቅድሚያ ተስጥቷቸው ሊከናወኑ የሚገባቸውን መስኮች በጋራ በመለየት ወደ ስራ ለመግባት ተስማምተዋል።

 

Please follow and like us: