የአፋር ክልል የወጣቶች ምክር ቤት በይፋ ተቋቋመ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር የአፋር ክልል የወጣቶች ምክር ቤትን አቋቋሙ። ምክር ቤቱ ወጣቶች በመደራጀት መብትና ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን እንዲያረጋግጡና በአገር ግንባታ ሂደት ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ያስችላል ተብሏል።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ የሺወርቅ አያኔ ወጣቶች ከሌላው ማህበረሰብ የተሻለ ለሀገር ልማትና ለፍትህ፣ ለእኩልነት የላቀ አበርክቶና አቅም አላቸው ብለዋል። በመሆኑም ወጣቶች በአገሪቱ ልማትና እድገት ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ በሁሉም ክልሎች የወጣቶች ምክር ቤት መመስረት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

የምክር ቤቱ መቋቋም ወጣቶች በሚያጋጥማቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፉና ድምፃቸውን እንዲያሰሙ በራሳቸው ጉዳይ ላይ እራሳቸው እንዲወስኑና ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ የሚያስችል ተጨማሪ ዕድልን እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚና አባላት ለወጣቱ የተሻለ ተጠቃሚነት በላቀ ተነሳሽነትና ትጋት እንዲሁም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩም በአጽዕኖት አሳስበዋል።

 

የአፋር ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዑመር ኑር አርባ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ውጤታማ እንዲሆን የተጀመረው ድጋፍና እገዛ እንደሚጠናከር ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ወጣት ኢንጂነር ኢብራሂም መሀመድ በክልሉ በሚካሄዱ የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ወጣቱ ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራን ብሏል። በመርኃ ግብሩ ላይ የፌዴራል እና የክልል የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የተቋቋመው የአፋር ክልል ወጣቶች ምክር ቤት አባላትና ስራ አስፈፃሚዎችም ቃለ መሀላ ፈፅመዋል።

የወጣቶች ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በጅግጅጋ፣ በሀረር፣ በድሬዳዋና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተመሰረተ ሲሆን የሰመራው 5ኛው መሆኑን ተጠቁሟል።

 

Please follow and like us: