የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ የትኩረት ነጥቦች

ማህበራዊ ጥበቃ በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ድህነትን፣የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋት ተጋላጭነትንና መገለልን ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ በመውሰድ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የተመጣጠነ እድገትን በማረጋገጥ ላይ የሚያተኩር የማህበራዊ ፖሊሲ ማዕቀፍ አካል ነው፡፡ ፖሊሲው በዋናነት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተቀናጀ ሁኔታ ጥበቃ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ዜጎች ለተለያየ ችግሮች እንዳይጋለጡ ለመከላከል፣ ዘርፈ ብዙ የማህበራዊ ዋስትና ስርዓትን ለመዘርጋት፣ የዜጎችን ሰርቶ የማግኘትና ጥሪት የመያዝ አቅምን ለማጎልበት፣ የስራ እድልንና የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል የተዘጋጀና ለጥቃትና በደል ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የህግ ጥበቃና ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተዘጋጀ ብሔራዊ ሰነድ ነው ፡፡

በሃገራችን የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን ለማረጋገጥ የተዘረጉ የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞች ስንመለከት በዋነኛነት በአቅርቦትና በተደራሽነት ረገድ ያለውን እጥረት በማቃለል የመላውን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል በድህነትና በተጋላጭነት ውስጥ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚዘረጉ አገልግሎቶች አቅርቦትና ተደራሽነት በተፈለገው መጠን ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚያግዷቸው በርካታ መሰናክሎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ፍላጎትንና አቅርቦትን በማመጣጠን ረገድ  የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል የማህበራዊ ጥበቃ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢና ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሲሆን በውጤቱም እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ የማህበራዊ ጥበቃ አፈጻጸም – መሰረታዊ አገልግሎቶችን በመስጠትና በወቅታዊ ድጋፍ ላይ ብቻ ሳይወሰን የማህበረሰብ ተሳትፎንና ንቅናቄን በማጠናከር እና የተቀናጀ ስርዓት በመዘርጋት በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩትን ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሰብዓዊ መብቶች ከማስጠበቅ  ባሻገር የተሸጋጋሪነት ባህርይ ያላቸውንና በህብረተሰቡ ውስጥ የሚታዩትን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተጠቃሚነት ልዩነቶችንና አለመመጣጠንን ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ያካትትል፡፡

በፖሊሲው ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት፣ ሴቶች ፣አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ሰርቶ ለማደር ጉልበትና አቅም የሌላቸው ግለሰቦች፣ ስራ እጦችና በተለያዩ የማህበራዊ የተፈጥሮና ሌሎች ምክንያቶች ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ፖሊሲው የማህበራዊ ጥበቃን በማቀናጀት እና በማስተባበር የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ማዕቀፍ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በፌዴራል፣ በክልል እና በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አደረጃጀቶችና መዋቅሮች ውስጥ የሚኖራቸውን ተግባራት፣ ሃላፊነቶችና የቅንጅትና የትብብር ስርዓት በግልጽ የሚያመለክት ነው፡፡ ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው ራዕይ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደህንነትና ዋስትና ተጠብቆ የማህበራዊ ፍትህ ሰፍኖ ማየት ሲሆን በፖሊሲው ስጥ የሰፈሩ ተልዕኮዎችን ስንመለከት ደግሞ ማህበራዊ ድጋፍ ማድረግና የዜጎችን መሰረታዊ የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶችንና ተጠቃሚነትን ማሳደግ ፣ የማህበራዊ መድን አገልግሎቶች ሽፋንና  ገቢ የሚያስገኙ ስራ እድሎችን ማስፋፋት እንዲሁም አግባብነት ያላቸው ህጎች ፣ደንቦች ፣መርሃ ግብሮች ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚያስችሉ ተቋማዊ አደረጃጀቶች ማዋቀርና ማጠናከር በተለይም ድሃና ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ከሃገሪቱ እድገት ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ናቸው፡፡

በፖሊሲ ሰነዱ ውስጥ አምስት የትኩረት መስኮች የተለዩ ሲሆን እነእርሱም የስራ እድልና የኑሮ ሁኔታን ማሻሻል፣ የማህበራዊ መድን አገልግሎትንና ልማታዊ ሴፍቲኔትን  ማስፋፋት የመሰረታዊ አገልግሎትንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግና ለጥቃትና ለበደል ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች የህግ ጥበቃና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ናቸው፡፡ ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ በውስጡ ያካተታቸው የማህበራዊ ጥበቃ እርምጃዎች ዘርፈ ብዙና በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ በማህበረሰብና በእምነት ተቋማት የሚተገበሩ በመሆናቸው ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች ደረጃ መለኪያ ያልነበራቸውን፣ በሽፋንና በተደራሽነት ፣ በፕሮግራሞች ተደጋጋፊነት ፣ በአደረጃጀት፣ በመረጃ አያያዝና ልውውጥ እንዲሁም በአስፈጻሚ አካላት የቀጥታና የጎንዮሽና የቅንጅት ስራዎች ክፍተት የነበረባቸው መሆኑን በመገንዘብና በጥናት በመለየት ክፍተቶቹን ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ፖሊሲው ማህበራዊ ጥበቃን ከማስፈን ባሻገር ለድህነትን ተጋላጭነትንና አድልዎና መገለልን በመቀነስ፣ በድህነት ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ከፋ ድህነት እንዳይገቡ በመከላከል ፣ የሰው ሃብት ልማትንና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ፣ ማህበራዊ ፍትህንና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ብሔራዊ ስሜትን ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው ፡፡

የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት የህብረቱን የማህበራዊ ፖሊሲ ማዕቀፍ ከልማት አጀንዳዎቻቸውና ስትራቴጂዎቻቸው ጋር በማቀናጀት ስር የሰደደውን ድህነትና ተጋላጭነቱን በመቀነስ የሃገሮችን ልማት ፍትሃዊና የተረጋጋ ለማድረግ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ወሳኝና ተመራጭ መሆኑን አምነውበትና ተስማምተውበት ወደ ስራ መግባታቸው በአህጉር ደረጃ የተሰጠውን ትኩረት ያመላክታል ፡፡ በዚህ መሰረት መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በቅንጅት በመስራት በፖሊሲው ላይ የተመለከቱ ግቦችን ፣መሰረታዊ መርሆዎችን፣ የትኩረት አቅጣጫዎችንና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎችን በጥልቀት በመገንዘብ በኢኮኖሚ ድቀት፣ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተጎዱና ልዩ ድጋፍ ለሚያሻቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዘላቂነት ያለው ድጋፍ በመስጠትና የማህበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማስፋፋት በጋራ እንድንረባረብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪ ያደርጋል፡፡

በዓለማየሁ ማሞ

ምንጭ ፡- ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ – ህዳር /2007 አዲስ አበባ

 

Please follow and like us: