የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከዩኤንኤድስ (UNAIDS) ሪጅናል ዳይሬክተር አን ሙዞኒ ጋር ተወያዩ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭነት የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመከላከል አኳያ በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከዩኤንኤድስ (UNAIDS) ሪጅናል ዳይሬክተር አን ሙዞኒ እና ልዑካን አባላቱ ጋር ውይይት አካሄዱ።

በውይይቱም፥ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ሁለንተናዊ መብት ለማስከበር፣ ማህበራዊ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ፣ በየደረጃው ያላቸውንም ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል። የሴክተሩ ባህሪ ዘርፍ ዘለል መሆኑንና የእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ በሌሎች አስፈጻሚ ተቋማት እቅድ ውስጥ እንዲካተትና ተፈጻሚ እንዲሆንም ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት፣ የወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ መስራት እንዲሁም የልጃገረዶች ትምህርትና የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ተደራሽነትን ማስፋፋት የኤችአይቪ ስርጭትን ለመግታት ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ከዚህ አኳያ የስርዓተ ጾታ ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱ እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያግዝ ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ተነድፎ በስራ ላይ መዋሉንም ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ገልጸዋል።

ጥቃትን ጨምሮ በግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ለመደገፍ እና መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ ያለመ ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከማህበራዊ ጥበቃ ጋር በተያያዘም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑትን ዜጎች ለመደገፍ ከሚተገበረው የሴፍተኔት ፕሮግራም ጋር በማስተሳሰር የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭት የመከላከል ስራ መስራት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

እንደሀገር የፖሊሲ አቅጣጫ መቀመጡ፣ የአሰራር ማዕቀፎች መኖራቸው፣ መዋቅር መዘርጋቱ፣ የማህበረሰብ አደረጃጀቶች መቋቋማቸው እንዲሁም በየዘርፋ የተለያዩ ፕሮግራሞች ተቀርጸው በመተግበር ላይ መሆናቸው የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭት የመከላከል ተግባርን በተሟላ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል።

የዩኤን ኤድስ (UNAIDS) ሪጅናል ዳይሬክተር አን ሙዞኒ በበኩላቸው፥ ዩኤንኤድስ ስርዓተ ጾታ ከኤችአይቪ ጋር ያለውን ትስስርና ስርጭቱን በመግታት ረገድ ያጋጠሙ ክፍተቶችን በጥናት መለየቱን ዳይሬክተሯ ገልጸው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከወረዳ ጀምሮ ትኩረት በመስጠት መሰራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ዳይሬክተሯ አድንቀዋል፤ በተለይ ከስርዓተ ጾታ ጥቃት መከላከልና ምላሽ መስጠት ጋር በተያያዘ ለሚወጣው ፖሊሲ ስኬታማ ትግበራ በደቡብ አፍሪካ በስራ ላይ የዋለውን ስትራቴጂ በተመለከተ ተሞክሮውን እንደሚያካፍሉ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሯ አክለውም፥ በተለይ የታዳጊ ህጻናትን፣ የወጣት ሴቶችንና የወጣቶችን በቫይረሱ መያዝ ለመከላከል ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ውይይት መደረጉ የሚታወስ ሲሆን በዚሁ መሠረት ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድን በማቋቋም እና ቅድሚያ ተስጥቷቸው ሊከናወኑ የሚገባቸውን መስኮች በጋራ በመለየት ወደ ስራ ለመግባት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

Please follow and like us: