የቤጂንግ መግለጫ እና የድርጊት መርሀ ግብር 30ኛ ዓመት ሀገር አቀፍ ግምገማና ሪፖርት ዝግጅት ሂደት ላይ ውይይት ተካሄደ

የቤጂንግ መግለጫ እና የድርጊት መርሀ ግብር 30ኛ ዓመት ሀገር አቀፍ ግምገማና ሪፖርት ዝግጅት ሂደት ላይ የአስተባባሪና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እና ሴቶችን ለማብቃት የተነደፈውን የቤጂንግ ስምምነት ተቀብላ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እየተሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የቤጂንግ ስምምነት 12 የትኩረት መስኮችን ያቀፈ መሆኑንና በዋነኝነትም ሴቶች ከሰላም፣ ከጤና፣ ከአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት፣ ከትምህርትና ስልጠና፣ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ ከሚዲያ ተሳትፎ፣ ድህነትን ከመቀነስ፣ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ሀገራት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ይህን መነሻ በማድረግ ሀገራችን ኢትዮጵያ በየአምስት አመቱ የተከናወኑ ተግባራትን የተመለከተ የአፈጻጸም ሪፖርት እያዘጋጀች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስታቀርብ መቆየቷን አስታውሰዋል።

እስካሁን በተደረገው ጥረትም በተለይም ደግሞ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢፌዴሪ መንግስት በወሰደው እርምጃ የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ሚናና የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ እንዲሁም ጥቃትን በመከላከል እና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በማሰፋፋት ረገድ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

6ኛው ዙር ሀገራዊ ሪፖርትም ሴቶችን በየዘርፉ ተሳታፊና እኩል ተጠቃሚ ከማድረግ ብሎም ሴቶችን ከማብቃት አኳያ ባለፉት አምስት አመታት የተከናወኑ ተግባራትን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ባካተተ መልኩ ማዘጋጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመወያየትና መረጃ ለመለዋወጥ መድረኩ መዘጋጀቱን  አስገንዝበዋል።

ሪፖርቱ ሀገር አቀፍ እንደመሆኑ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከየተቋማቸው አንጻር ባከናወኗቸው ተግባራት ዙሪያ ተጨባጭ መረጃዎችን በመስጠት እንዲተባበሩና ከኮሚቴው ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ በአጽዕኖት አሳስበዋል።

በመድረኩ የቤጂንግ መግለጫ እና የድርጊት መርሀ ግብርን ጨምሮ የቤጂንግ+30 ሀገር አቀፍ ግምገማና ሪፖርት ይዘትና የዝግጅት ሂደት በተመለከተ በዩኤን- ውመን ፕሮግራም ስፔሻሊስት እና የክብርት ሚኒስትር አማካሪ ወ/ሮ ቤዛዊት በቀለ አጭር ገለጻ ተደርጓል።

እንዲሁም በሪፖርት አዘገጃጀት የድርጊት መርሀ ግብር ዙሪያ የአማካሪ ድርጅት ተወካይ ማርታ ነመራ ማብራሪያ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፤ በበለይ በስትሪንግ ኮሚቴ አስተባባሪ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በውይይት መድረኩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የሲቪክ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

 

 

Please follow and like us: