ከ1600 በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች  የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ (Prosthetic Orthotics)  አገልግሎት ማግኘታቸው ተገለፀ ።

ከ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2016 ጀምሮ በ 4 ዙር  በተከናወኑ የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ከ1600 በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን  የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ (Prosthetic Orthotics)  አገልግሎትን ከ ጃፑር ፉት ማግኘታቸው ተገለፀ ።

ይህ የተገለጸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ (Prosthetic Orthotics)  አገልግሎትን በጃፑር ፉት(Jaipur Foot)   አማካኝነት ሲያስተባብሩ ለቆዩት አምባሳደር ሳቲሽ ማሀታ    ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ የምስጋናና የእውቅና መርሀግብር ወቅት ነዉ ።

በስነስርዓቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስተር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት ይህንን የምስጋናና እውቅና መርሀግብር ማድረግ ያስፈለገው አምባሳደር  ማሀታ  በተለያዩ ክልሎች ከህንድ መንግስትና ከ ዣፑር ፉት (Jaipur Foot) ጋር በመሆን የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው   ለብዙ አካል ጉዳተኛ ወገኖቻችን ዳግም ተስፋንና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ የመስራት ፣የመኖርና የስነ ልቦና ጫናን በመቀነሰ  ሂደት ውስጥ ላበረከቱት አስተዋፅኦ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሯ አክለውም ይህ አይነቱ ድጋፍ ለማህበረሰቡ ከሚሰጠው የላቀ አስተዋፅኦ በተጨማሪ መንግስት እንደ ሀገር ለጀመራቸው አካል ጉዳተኞችን የማካተት ፣ሰብአዊ ክብራቸውን የመጠበቅና ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎች ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር አላማን እንደሚያግዝ ገልፀዋል ።

አምባሳደር  ሳቲሽ ማሀታ በበኩላቸው በተደረገላቸው የእውቅናና የምስጋና መርሀ ግብር መደሰታቸውን ገልፀው ይህ አይነቱ ትብብርም እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል ።

የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ (Prosthetic Orthotics)  አገልግሎት እስካሁን በመቀሌ ፣ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ፣አዲስአበባና በአፋር ክልሎች እ.አ.አ ከ2016 ጀምሮ ከህንድ በመጡ ባለሙያዎች ተሰጥቷል ።በአሁን ሰአትም በ አፋር ክልል ሎጊያ ሆስፒታል በመሰጠት ላይ ይገኛል።

 

Please follow and like us: