የ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የስምሪት መርሐ-ግብር የዝግጅት ስራ ተጀመረ።

የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት  የስምሪት መርሐ-ግብር የዝግጅት  ስራዎችን በተመለከተ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የወጣቶች ዘርፍ አመራሮች ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሳታፊ ወጣቶች ቁጥር፣ በህብረተሰብ ተጠቃሚነት እና አገልግሎቱ በገንዘብ ሲተመን ባለፉት ዓመታት መልካም አፈጻጸም የታየበት መሆኑን ገልጸው በዚህም የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  ክፍተቶችን በመሙላት በርካታ ውጤቶች እንደተመዘገቡ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ አገልግሎቱ በወጣቶችና በማህበረሰቡ ዘንድ ባህል እንዲሆን ለማስቻል እንዲሁም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት /GDP/ ያለውን አበርክቶ ለመለካት የሚያስችሉ ፖሊሲ፣ የህግ እና የአሰራር ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰው ለመጪው የ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የስምሪት መርሐ-ግብር ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውና ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበለጸገው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተዳደር የመረጃ ስርዓት ዝርጋታ /Youth Volunteer Management Information System/ የ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የስምሪት መርሐ-ግብር መነሻ እቅድ እንዲሁም የወጣቶች ወሰን ተሸጋሪ እና ድንበር ተሸጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአተገባበር ማኑዋል ረቂቅ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን የመረጃ ስርዓት ዝርጋታ፣ መነሻ ዕቅዱንና የአተገባበር ማኑዋሉን ለማዳበር የሚያስችሉ ግብዓቶችን ማሰባሰብ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለክልሎች የሚያደርገውን የክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥልና የተጀመሩ የህግ እና የአሰራር ስርዓቶች ተጠናቀው በአፋጣኝ ወደ ትግበራ እንዲገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ተጨማሪ ገለጻ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ምላሽና  ማብራሪያዎች ተሰጥቶበታል። የቀጣይ አቅጣጫ በማቅረብ መድረኩ ተጠናቋል።

Please follow and like us: