በጋምቤላ ክልል  ለተከሰተው ግጭት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ጋር አፋጣኝ የሰብአዊ ምላሽ መስጠት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያየ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስተር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ከዩኒሴፍ የመጡ ልዑካንን በጋምቤላ ክልል ጆሬ ወረዳ በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ለተከሰተው ግጭት አፋጣኝ የሰብአዊ ምላሽ መስጠት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ሚኒስትሯ እንደገለፁት በጋምቤላ ጆሬ ወረዳ  በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ እና ሰብአዊ ድጋፍ የሚሹ 6100  ዜጎች መካከል ነብሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች፣ህፃናት፣ አረጋውያንን ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል። አክለውም በአካባቢው የነበረው  የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫን ጨምሮ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በመፍረሳቸው ህፃናትና ሴቶች ከምግብ በተጨማሪ ሌሎች የስነልቦና ድጋፎችም እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ማሪ ኮ በበኩላቸው የዩኒሴፍ የጋምቤላ መስክ ጽህፈት ቤት ግጭቱ ከተከሰተ ወዲህ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጋር በጋራ በመሆን ሀብት በማሰባሰብ በሚኒስትሯ የተነሱ ተጨማሪ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

 

Please follow and like us: