የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ::

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር ተፈራረመ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት ስምምነቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ፖሊሲ፣ ህግና ስትራቴጂን የማመንጨትና የመቅረጽ አቅሙን ለመገንባት፣ የፍልሰተኞችና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ በፖሊሲ፣ በህግ፣ በስትራቴጂና በብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ፣ የፍልሰት ተመላሾችን፣ የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችንና የፆታ ጥቃት የደረሰባቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም እንደሚረዳ ገልፀዋል ።

በተጨማሪነትም ስምምነቱ ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የጋራ ጥረት እና የተቀናጀ ፕሮግራም ለመቅረጽ አስቻይ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

አክለውም መንግስት የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለመግታት የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል ።

ለዚህም በቅርቡ ይፋ የሚደረገው የአምስት ዓመት እቅድ አንዱና ዋነኛው ከዓለም የፍልሰት ድርጅት ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነትም ቀደም ሲል በቅንጅት የሚሰሩ ተግባራትን ለማጠናከርና ለቀጣዩ የአምስት አመት እቅድ አተገባበር የጎላ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋኔ-ፎል በበኩላቸው በየትኛውም አገራት የሚገኙ ሰዎች ህገ-ወጥ ስደትን እንደ አማራጭ መውሰድ መጀመራቸውን ጥናቶች ማመላከታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ለመሸጋገሪያነት አመቺ ናቸው ተብለው በሚታመኑ አገራት የፍልሰተኞች ቁጥር እንደሚጨምር ጠቁመው በዚህም ስደተኞች ለተባባሰ ችግር የሚዳረጉባቸው እድሎች ሰፊ መሆናቸውን አክለዋል።

በመሆኑም በፍልሰትና የስደተኞች ደህንነት ማረጋገጥ ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በርብርብ በመስራት ጉዳቱን መግታትና ማስቆም ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ችግሩን ለማቃለል የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው ድርጅታቸው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

Please follow and like us: