የቻይና ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ቢሮ የተመሰረተበት አምስተኛ አመትና የቻይና ኢንተርፕራይዞች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሔደ

በመርሐ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት ቻይናና ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና ፖለቲካ ዘርፍ ለአመታት የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰዋል።

የቻይና ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንትም የዚሁ ዘመናትን የተሻገረ የእርስ በርስ ጠንካራ ወዳጅነትና ትብብር ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

ሚኒስትሯ እንደገለፁት የቻይና ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት ሰብዓዊነት ድንበር እንደሌለው ያሳየ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ፕሮጀክት እስከ ፈረንጆቹ 2023 መጨረሻ 10 ነጥብ 54 ሚሊየን ዶላር ወጪ በማድረግ 320 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ሲያበረክት ለቆየው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ከፋውንዴሽኑ ጋር የሴቶችን፣ ህጻናትን እና ሌሎች ተጋላጭ ወገኖችን ፍላጎት ለማሟላት ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት በትብብር ውይይቶች መጀመራቸውን ገልፀዋል። ከውይይቱም ፍሬያማ የአጋርነት ስምምነቶች ላይ እንደሚደርሱም ፍንጭ ተሰጥተዋል ።

 

 

በመርሐ ግብሩ ላይ የፋውንዴሽኑ ዋና ዳይሬክተር ዋንግ ጀን ባደረጉት ንግግር÷ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ፕሮጀክት እንዳለው ገልጸዋል።

 

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ኮንስለር ሚስትር ያንግ ይሃንግ÷ ቻይና በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ በዋናነት ድህነትን በማጥፋት፣ ረሃብን ዜሮ በማድረግ፣ የንጹህ ውሃ ተደራሽነትን በማስፋትና ጤናማ ማህበረሰብን በመፍጠር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑ በመርሀግብሩ ላይ ተጠቅሷል።

Please follow and like us: