“የሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በወጣቶች ስኬት ላይ በመሆኑ ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ በጋራ መስራትና መረባረብ ያስፈልጋል” – ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር በተዘጋጀ መድረክ በወጣቶች ዙሪያ የሚሰሩ የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ዛሬ በይፋ ተመሰርቷል።

በፎረም ምስረታ መርሀ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዋ ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ እንደተናገሩት፤ ወጣቶች ህልም አላሚዎች፣ አዳዲስ ነገር ፈጣሪዎች፣ የዛሬና የነገ መሪዎች ናቸው ብለዋል። በወጣቶች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የወጣቶችን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ብሎም የበለፀገች፣ ሁሉን አቀፍ እና ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ እንደሆነም አንስተዋል። እስካሁን ወጣቶች በየዘርፉ የሚገጥማቸውን ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ ለራሳቸውና ለሀገራቸው ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዲችሉ በመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተናጠል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በወጣቶች ስኬት ላይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ በጋራ መስራትና መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል። የጥምረት ዋነኛ ዓላማም የስራ ድግግሞሽን በማስቀረት በወጣቶች ዙሪያ የሚሰሩ ስራዎችን በቅደም ተከተል ለመፈጸም እንዲሁም ተቋማቱ በስቴራቴጂና በፕሮግራሞቻቸው ውስጥ ወጣቱን የተመለከቱ ጉዳዮችን በተገቢው መልኩ አካተው እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል። በተጨማሪም በመንግስትና በአጋር አካላት መካከል ትበብርና ቅንጅትን ለማጠናከር፣ ሀብትን በጋራ ለማሰባሰብ ከፍ ሲልም በተደመረ አቅም ለውጥ በማምጣት የሀገራችንን ወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነም ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ በወጣቶች ዙሪያ ከሚሰሩ አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አረጋግጠዋል። ለፎረሙ ስኬታማነትም ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲሰራ በአጽዕኖት አሳስበዋል። መድረኩ የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል። የፎረሙ የቴክኒክ ኮሚቴ አባልና የከፍታ ፕሮጀክት አማካሪ ዶ/ር የሺጥላ ክፍሌ ጥምረቱን በዘላቂነት ማጠናከርና ስራዎችን ውጤታማ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል። በዕለቱ የፎረሙን የስራ እንቅስቃሴ የሚመሩ የአብይ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ተካሂዷል።

Please follow and like us: