የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። “የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተጠናከረ ቅንጅታዊ አሰራር ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ከወጣት መር እና ወጣት ተኮር ድርጅቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ዘርፍ አስተባባሪ መለሰ አለሙ እንዳሉት ወጣቶችን በሀገር ዕድገትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለማሳተፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በተለይ በወጣቶች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች የወጣቶችን ተሳትፎ በሁሉም መስክ ለማሳደግ የሚሰሩትን ስራ የበለጠ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል። መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሚያከናወኑት ስራ ምቹ መደላድል መፍጠሩንም ገልጸዋል። በዚህም የወጣቶች ፍላጎት እንዲሟላ እና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሳካ ቅንጅታዊ ስራ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የሲቪክ ምህዳሩ መስፋቱን ገልጸዋል። ባለስልጣኑ ለድርጅቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በመጠቆም በተጨማሪ የተቋቋሙበትን ዓላማ መሰረት በማድረግ መስራታቸውን እየተከታተለና እየተቆጣጠረ መሆኑን ተናግረዋል።የሀገሪቱ ዕድገትና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባል ያለው ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ገና ነው። በዚህም ለነገ የተሻለች ሀገር ለመፍጠር በጋራ መስራት አለብን፤ ለዚህም የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት በወጣቶች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ተወካዮች በበኩላቸው የወጣቶችን ችግር ለመፍታት እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቁመዋል። ድርጅቶቹ ከመንግስትና ከምክር ቤቱ ጋር በመተባበር የሚፈለገወን ለውጥ ለማስመዝገብ እየሰራን ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

Please follow and like us: