የኢትዮጵያ የወጣቶች የሰላምና ደህንነት የድርጊት መርሀ ግብር ዝግጅት ሂደት ላይ ያተኮረ የልምድ ልውውጥና ስልጠና ተካሄደ።

የተባባሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣውን የወጣቶች የሰላምና የደህንነት ሪዞሉሽን እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የወጣቶች ሰላም እና ደህንነት ማእቀፎችን ብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብር ለማዘጋጀት የሚረዳ የልምድ ልውውጥና ስልጠና የሴቶችናማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን አካሄደ።

በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያረጉት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወ/ሮ የሺወርቅ አያኔ እንደገለጹት የአንድን ሀገርን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥና ለውጥ ለማምጣት በሚሰሩ ስራዎች ላይ ወጣቶችን በንቃት ማሳተፍና ባለቤት ማድረግ ለአንድ ሀገር ለዘላቂ ልማትና ትውልድ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ጠቅሰዋል። አማካሪዋ እንደገለፁት ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ ሁለንተናዊ ብቃት ለማጎልበት የሚያስችሉ በሀገር አቀፍ፣ አህጉራዊና አለም አቀፍ የተለያዩ ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ ስምምነቶች በስራ ላይ መዋላቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ወጣቶች በሰላም ድርድር እና ስምምነቶች ውስጥ እንዲሳተፉ እና ድጋፍ እንዲሰጡ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ሚናቸውን ማጉላትና ዓለም አቀፍ የውሳኔ ማዕቀፍ ውስጥ ወጣቶችን በማብቃት በሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። አክለውም ይህንን የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላምና ደህንነት የድርጊት መርሀ ግብር እየተከለሰ ካለው ከብሄራዊ የወጣቶች ፓሊሲ ጋር በማጣጣም የረዥም ጊዜ ሰላም፣ መረጋጋት እና የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ለመማረጋገጥ አስተዋፅዖ ያደርጋል ብለዋል።

በዕለቱ የተገኙት በዩ.ኤን.ዲ.ፒ የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና ሰላም ግንባታ ቡድን መሪ አቶ ፍስሐ መኮንን እንደገለፁት የልምድ ልውውጥና ስልጠናው አላማ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቴክኒካል ሰራተኞች ጠቃሚ እውቀት እና ልምድ አግኝተው ለኢትዮጵያ ውጤታማ የወጣቶች የሰላምና ደህንነት የድርጊት መርሀ ግብር ማጎልበት ሂደት ለመፍጠር እንደሆነ ጠቅሰዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወጣቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ያላቸውን ሚና እና በሂደቱም እንዲሳተፉ የተደረጉ ጥረቶችን፣ ያሉ ምቹ ሁኔታዎች እና ተቋማዊ አሰራርን ያመላከተ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አጽድቆ ሥራ ላይ ያለው UNSR2250 ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በተጨማሪም የተለያዩ ሀገራት ልምድ በብሔራዊ ድርጊት መርሀ ግብሩ አዘገጃጀት፣ አተገባበር እና በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረትም እየሰራ ያለውን ስራዎች ሀገራትም መርሀ ግብር እንዲያዘጋጁ የተሄደበትን ርቀት ያመላከተ ልምድ በመውሰድ ኢትዮጵያም ከዚህ ልምድ በመውሰድ ያሳየችው ተነሳሽነት ጥሩ መሆኑ በልምድ ልውውጡ ወቅት ተጠቅሷል፡፡

 

Please follow and like us: