ብሔራዊ ረቂቅ የወጣቶች ፖሊሲ ዘመኑን የዋጀ – የወጣቶችን ፍላጎት፣ ጥያቄና ተግዳሮት ሊፈታ በሚችል አግባብ እየተዘጋጀ ነው

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከየኢትዮጵያ ሴቶችና ህጻናት ልማት ድርጅት ጋር በመተባበር ብሔራዊ የወጣቶች ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ግብዓት የማሰባሰቢያ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ በወጣቶች ልማት ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እየተሳተፉ ይገኛል። በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወ/ሮ የሺወርቅ አያና በዚሁ ጊዜ፥ ፖሊሲው ባለፉት 20 ዓመታት ለወጣቶች መልካም አጋጣሚዎችንና ዕዶሎችን የመፍጠሩን ያህል በርካት ክፍተቶች እንደነበሩበት በተካሄደ የግምገማ ጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል። በመሆኑም ካለፈው የፖሊሲ ትግበራ ትምህርት መውሰድና መልካሙን ማጠናከር ይገባል ያሉት አማካሪዋ የሌሎች ሀገራትን ልምድና ተሞክሮ በመፈተሽ እንዲሁም ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ ተቃኝቶ መከለስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል። ለዚህም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በአማካሪ ድርጅቶች እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባቋቋመው ቴክኒክ ኮሚቴ አማካኝነት ጥናትና የረቂቅ ሰነድ ዝግጅት እየተካሄደ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፤ አጥኚ ቡድኑን እና ለጥናት ሂደቱ ድጋፍ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።

ፖሊሲው ዘመኑን የዋጀ፥ አሁን ላይ ያለውንና የወደፊቱን የወጣቶች ፍላጎት፣ ጥያቄና ተግዳሮት ሊፈታ በሚችል አግባብ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ የሺወርቅ ፖሊሲው ከመጽደቁ በፊት በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻና አጋር አካላት ግብዓት እንዲሰጡበት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አጋር አካላት እንደመሆናቸው መጠን በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ግልጽ ግንዛቤ እንዲይዙበት እና መካተት ያለባቸውን በመለየት ሰነዱን ለማዳበር የሚያግዙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲያመላክቱ ታስቦ መድረኩ መመቻቸቱን አማካሪዋ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶችና ህጻናት ልማት ድርጅት ዳይሬክተር አቶ አያሌው እጅጉ እና የራይት ሂር ራይት ናው(RHRN2) ኮንሰርቲየም አስተባባሪ ወ/ሮ ፍሬህይወት ተስፋዬ በበኩላቸው በአፍላ ወጣቶች፣ በወጣቶች ስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት፣ በልጃገረዶች ትምህርትና ንጽህና አጠባበቅ ዙሪያ እየሰሯቸው ያሉ ተግባራትን አስረድተዋል። በፖሊሲው ላይ ግብዓት ለመሰጠት ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ፖሊሲውን መከለስ ስለአስፈለገበት መነሻ ምክንያት፣ ቀደም ሲል ከነበረው በምን እንደሚለይ፣ በፕሮግራም እና ንዑስ ፕሮግራም ደረጃ ስለተካተቱ አንኳር ጉዳዮች እንዲሁም ስለትግበራ ስልቱ በጥናት ቡድኑ አባላት በፕሮፌሰር በላይ ተፈራ፣ ዶ/ር መለሰ ጌቱ እና ዶ/ር በፍቃዱ ዘለቀ በዝርዝር ተብራርቷል።

በመድረኩ በተለይም የወጣቶች ስብዕና ልማት ግንባታ፣ የወጣቶች ትምህርት፣ የወጣት ማዕከላት አገልግሎት፣ ከወጣቶች ሰነተዋልዶፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ትርጉም ያለው ተሳትፎን ማረጋገጥ፣ የተጠያቂነት አሰራር ማስፈንን የሚሉ እና የተመለከቱና ሌሎችም ጉዳዮች በሰፊው የተዳሰሱ ሲሆን ትኩረት በሚሹ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ በጥናት ተሳታፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

 

Please follow and like us: