ብሔራዊ የህጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝ ስርዓት ይፋ ሆነ

ብሔራዊ የህጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝ ስርዓት በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል።

የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን ይፋ ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ቀደም ሲል የነበረው የመረጃ አያያዝ የህፃናትን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ክፍተት እንደነበረበት አስታውሰዋል።ክፍተቶችን ለማስወገድና ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ሲባል ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ የህጻናት ጥበቃ የመረጃ አያያዝ ስርዓት /CPIMS+/ ይህ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ይፋ እንደተደረገ ተናግረዋል። ዲጂታል የመረጃ ስርዓት መዘርጋቱ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህጻናትን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ይረዳል፤ ፈጣንና ቀልጣፋ የቅብብሎሽ ስርዓትን ለማጠናክርና ምላሽ ለመስጠትም የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር ለችግር ተጋላጭ ህጻናትን ቁጥር ለማወቅና የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለይቶ መረጃ ለመያዝ እና ተገቢውን ድጋፍ ለተገቢው ህጻን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ የህጻናትን ችግር ተጋላጭነትና አጋላጭ ምክንያቶችን በትክክል ለይቶ ለማስቀመጥና ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥ አኳያም የተሄደበትን የምላሽ አሰጣጥ ሂደት በግልጽ ለመረዳት ያስችላል ብለዋል። ይህን የህጻናት ጥበቃ መረጃ አያያዝ የዲጂታል ስርኣት ወደ ተግባር ለማስገባት በ8 ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ በተመረጡ ወረዳዎች የህጻናት ጉዳይ መረጃ አያያዝ ሙከራ ለማድረግና ወደፊት በሌሎችም ክልሎችና ወረዳዎች በስፋት ለማስጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ እንዲሁም አስፈላጊው ስልጠናና ቁሳቁስ የማሟላት ሰፊ ስራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ታደለ ቡርቃ በበኩላቸው ስርዓቱ የመረጃን ማዕከላዊነት፣ ታማኝነት፣ ተደራሽነትና ቀልጣፋነትን ከማሳለጥ እና የህጻናትን ጥቅምና ደህንነት ከማስከበር አንጻር ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። የመረጃ ስርዓቱን በዘላቂነት ለማጠናከርና እስከታች ተግባራዊ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት የቴክኒክ፣ የገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን ማጠናከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በዕለቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህጻናት ጉዳይ መረጃ አያያዝ ሲስተም አስተዳደር ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ቴዎድሮስ ወርቁ አዲሱን የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በተመለከተ ሙያዊ ገለጻ አድርገዋል።

በተጨማሪም በመድረኩ ጉዳዩን አስመልክቶ የፖናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን ሲስተሙን ተግባራዊ ለማድረግ ከአስፈጻሚ ክልሎችጋር የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ተካሂዷል።

 

Please follow and like us: