በተቋማት የሚገኙ የስርዓተ ጾታ አስፈጻሚ አካላትን አቅም ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሄደ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በፌዴራልና በክልል የሚገኙ የስርዓተ ጾታ አስፈጻሚ አካላትን አቅም ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በኢትዮጵያ የዩኤን ውመን ዳይሬክተር ሚስ ሲሲል ሙካሩበጋ ጋር ውይይት አካሂዱ።

በውይይቱም፥ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስርዓተ ጾታ እቅድ፣ ትግበራና የቁጥጥር ስርዓትን ለማሻሻል፣ የተቋማትን አቅም ለማሳደግ፣ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ስርዓቱን ለማጠናከርና ለማዘመን እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ የአካቶ ትግበራ ስርዓቱን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። ሆኖም በዘርፉ የእወቀትና ክህሎት ክፍተት፣ የሰው ሀይልና የመረጃ እጥረት እንዲሁም የሀብት ውሱንነት መኖሩን አንስተዋል። እነዚህን ችግሮችና የሚስተዋሉትን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያግዙ ፕሮጀክቶችን መቅረጽና ተግባራዊ ማይረግ እንዲሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በቀጣይም እንደሀገር በተቋማት ዘንድ የተጠያቂነት አሰራርን ለማስፈን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል። ሆኖም በዘርፉ የተቀመጡ ግቦች ውጤታማ እንዲሆኑ ቅንጅታዊ አሰራሩን ይበልጥ ማጠናከር እና በባለቤትነት መንፈስ በጋራ መስራት እንደሚገባ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ አጽዕኖት ሰጥተዋል። በዚህ ረገድ ዩኤን ውመን እያደረገ ላለው ጥረት አመስግነው፣ የተጀመሩ ስራዎች ዘላቂና ቀጣይነት እንዲኖራቸው ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የዩኤን ውመን ዳይሬክተር ሚስ ሲሲል ሙካሩበጋ በበኩላቸው ስኬታማ የፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም ትግበራ እንዲኖር ማስቻል ሴቶችና ልጃገረዶችን የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸው፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራትም አድንቀዋል። ወደፊትም ዩኤን ውመን የስርዓተ ጾታ እኩልነትና ሴቶችን ለማብቃት የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

 

Please follow and like us: