ለህጻናት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራትና ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ትውልድን ለማነጽ ብሎም ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ያስችላል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

ለህጻናት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራትና ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ትውልድን ለማነጽ ብሎም ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት እንደሚያስችል የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ። የአማራ ክልል በብሔራዊ ደረጃ ዘንድሮ ለ33ኛ ጊዜ “የኢትዮጵያ ህጻናትን የትምህርት ተሳትፎና ጥራት የማስጠበቂያ ጊዜው አሁን ነው!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘው የአፍሪካ ህጻናት ቀን የማጠቃለያ መርሀ ግብር አካሂዷል።

በፕሮግራሙ ላይ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፥ ትምህርት በእውቀትና ክህሎት የታነጸ፣ የተሟላ ሰብዕና ያለው፣ በምክንያት የሚያምን፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት የሚችል እንዲሁም በየዘርፉ ብቁ፣ ተወዳዳሪና አምራች ዜጋን ለማፍራት ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ ለህጻናት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራትና ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ትውልድን ለማነጽ ብሎም ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ያስችላል ብለዋል፡፡ የህፃናት ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ መሆኑን የገለጸት ክብርት ሚኒስትሯ በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ከትምህርት ገበታ የራቁ ህጻናት የትምህርት አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆኑ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም በአገራችን በህጻናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመተባበር የህፃናት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻልና የወደፊት ተስፋቸውን ለማለምለም በባለቤትነት መንፈስ እንዲረባረብና አቅም በፈቀደ መጠን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአማራ ክልል የገጠሙትን ተግዳሮቶች ተቋቁሙ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል፤ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አካላትንም አመስግነዋል። በዓሉን ምክንያት በማድረግ ህዝባዊ ንቅናቄ መካሄዱ የህጻናት ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው፣ ችግሮቻቸው ተገቢው ምላሽ እንዲያገኙና በዘላቂነት እንዲፈቱ ግንዛቤ ለመፍጠርና ህብረተሰቡ የመፍትሔው አካል ሆኖ እንዲንቀሳቀስ የበኩሉን አስተዋጾዖ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዱ ሁሴን በበኩላቸው፥ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋፋት ችግር የሆኑት ጉዳዮችን የምክንያትና ውጤት ትስስሮሹን በውል መለየትና መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በተለይ የህጻናትን የትምህርት ተሳትፎና ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ እንቅፋት የሆኑትን ግጭቶች ማስወገድ፣ ጥቃቶችን፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና የጉልበት ብዝበዛዎችን ማስቆም እንዲሁም የትምህርት መሠረተ ልማትን ማስፋፋትና ማጠናከር ይገባል፤ ለዚህም ደግሞ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

በዕለቱ በክልሉ በዓሉን አሰመልክቶ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ የፖናል ውይይት ተካሂዷል። እንዲሁም ለህጻናት ድጋፍና ክብካቤ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

Please follow and like us: