ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ለተገነባው ቤተ ህጻናት የህጻናት ማሳደጊያና መንባከቢያ ማዕከል የ1ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ለተገነባው ቤተ ህጻናት የህጻናት ማሳደጊያና መንባከቢያ ማዕከል የ1ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

የዘንድሮ የአፍሪካ ህጻናት ቀንን ምክንያት በማደረግ በአማራ ክልል የተከናወኑ የልማት ስራዎች ጉብኝት ተካሂዷል። በጉብኝቱ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የአማራ ክልል ምከትል ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር አቡዱ ሁሴን፣ የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት አለሚቱ ኡሞድ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የአማራ ክልል ምከትል ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር አቡዱ ሁሴን የክልሉ የሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር መተባበር በባህርዳር ከተማ ቀበሌ 14 ውስጥ በ27 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ዘመናዊ የህጻናት ማሳደጊያና መንባከቢያ ማዕከል መርቀው ከፍተዋል። የስራ ኃላፊዎቹ ቤተ ህጻናት የህጻናት ክብካቤና ድጋፍ ማዕከል እና በማዕከሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙ ህጻናትንም ተመልክተዋል።

በዕለቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ህጻናትና ወላጆችም ምግብ ነክና ሌሎች ድጋፎችም ተደርጓል። የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ በተቀናጀ አግባብ የተከናወኑ ተግባራትን አድንቀዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዲስ የተገነባውን ማዕከል በግብዓት ለማሟላት እንዲያስችልም የ1ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ድጋፋ ወደፊትም ቀጣይነት እንደሚኖረውም ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ  አስታውቀዋል።

 

Please follow and like us: