በዘንድሮ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ34ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ ተገለጸ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሰላም እና የትምህርት ሚኒስቴር “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብርን አስመልክቶ ለሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ በጋራ ሰጥተዋል።

በግለጫው፥ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ “አብሮነትን፣ የሀገርንና የትውልድ ግንባታን፣ ማህበራዊ ትስስርንና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር” ዓላማ አድርጎ በሚካሄደው የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብር ከ34 ሚሊዮን 274 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ዜጎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ50ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም በመንግስትና በማህበረሰቡ ያልተሸፈኑ ከ21ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የልማት ሥራዎችና ማህበራዊ አገልግሎቶች ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር፣ አብሮነትንና ሀገር ግንባታን ማጠናከር፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት መገንባትና ማደስ፣ ደጋፍ የሚሹ ወገኖችን መደገፍ፣ የደም ልገሳ፣ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት አገልግሎት፣ የሰላምና ጸጥታ፣ የማጠናከሪያ ትምህርትና ስልጠና፣ ሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረግና እና ሌሎች ዘርፎች በክረምቱ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው 14 የስምሪት መስኮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። የበጎ ፈቃደኝነት ግንዛቤና አስተሳሰብ በወጣቶችና በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲዳብር፣ የማህበረሰብ ትስስር እንዲጎለብት፣ ዜጎች ከሚኖሩበት አካባቢ ውጪ ያሉትን የማህበረሰቡን ጠቃሚ ዕሴቶች፣ ልምዶችና ባህሎች እንዲቀስሙ እንዲሁም ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትን ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን በየአካባቢው የሚከናወኑየበጎ ፈቃድ ተግባራትን ሽፋን በመስጠት እንዲሁም ህብረተሰቡን በንቅናቄ መርሀ ግብሩ በንቃት እንዲሳተፍ በማነሳሳት የበኩላቸውን እንዲወጡ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኸይረዲን ተዘራ በበኩላቸው፤ በንቅናቄ መርሀ ግብሩ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የህብረተሰቡን የአብሮነት እሴቶች እና ማህበራዊ ትስስሮሽን ለማጠናከርና በሀገረ መንግስት ግንባታ ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ በመግለጫው አንስተዋል።

በመርሀ ግብሩ 20ሺህ የሚጠጉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለይ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰማሩ ይደረጋል ያሉት በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጦሽኔ ናቸው። በንቅናቄው አቅም ለሌላቸው ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ እና የማጠናከሪያ ትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና ሌሎች በስብዕና ግንባታ ላይ ያተኮረ ሰፊ ስራ በቅንጅት እንደሚሰራ  አስታውቀዋል። መርሀ ግብሩ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በተቀናጀ አግባብ ተግባራዊ እንደሚደረግና ለዚህም ስራዎች በጋራ እየታቀደ  እየተገመገመ የሚሄድበት አሰራር መዘርጋቱን በመግለጫው ተመልክቷል።

 

 

Please follow and like us: