የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) ዘላቂነት ያለውና የስርዓተ ፆታ እኩልነት የተተገበረበት የአየር ትራንስፖርት እንዲኖር ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተገለጸ

የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) ዘላቂነት ያለውና የስርዓተ ፆታ እኩልነት የተተገበረበት የአየር ትራንስፖርት እንዲኖር ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተገለፀ፡፡ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) የስርዓተ ፆታ እኩልነት የተተገበረበት የአየር ትራንስፖርት መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄዷል።

በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታን በመወከል  መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ስለሺ ታደሰ እንደገለፁት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶችን ጉዳይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ በማካተት የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ገልፀው የዛሬውም መድረክ የዚሁ ሂደት አካል እንደሆነ በሰፊው አብራርተዋል፡፡ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ በማካተት የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ለዘላቂ ልማት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ሰላማዊና የተረጋጋ የስራ ደህንነት ለማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የኮሜሳ ሴክሬትሬት ወ/ሮ ቢትሪስ ሀምስንዴ በበኩላቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የልማት ፕሮግራሞችን ለማሳካት፣ በአህጉራችን የአቪዬሽን ዘርፉ ለማሳደግ እንዲሁም በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ብሎም በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ የአየር ትራንስፖርት ልማቱን በመደገፍ ላይ እንደሚገኝና ሴቶች በዚሁ ዘርፍ እንዲሳተፉና ዘላቂነት ያለው የአየር ትራንስፖርት እንዲኖር ለማስቻልበትኩረት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ለቀጣይ ሶስት ቀናት በሚካሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረክ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማትና በሀገራችን የአቪዬሽን ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን መድረኩ የስርዓተ ፆታ እኩልነት በአየር ትራንስፖርት ውስጥ ያለውን እጅግ ዝቅተኛ የሴቶችን ስምሪት ሊያሻሽል ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

Please follow and like us: