ሴቶች ወደ አቪዬሽን ዘርፍ እንዳይገቡ የሚከለክሉትን ተግዳሮቶች በጥናት መለየትና መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ተገለጸ

የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የስርዓተ ፆታ እኩልነት የተተገበረበት የአየር ትራንስፖርትን አስመልክቶ ሲካሄድ የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተጠናቋል፡፡

በማጠናቀቅያ ፕሮግራሙ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሁሉም ተቋማት ውስጥ የስርዓተ ጾታን እኩልነት በማካተት ሴቶችን በተለያዩ ዘርፎች ለማብቃት ከምንግዜውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። የስርዓተ ፆታ ጉዳይን በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ በማካተት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡ ኮሜሳም ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት በአጋርነት እየሰራ በመሆኑ ከልብ አመስግነዋል።

ሴቶችና ልጃገረዶችን ለማብቃትና ተሳትፎ ለማሳደግ ከሚወሰዱት እርምጃዎች አንዱ በትምህርት ዘርፍ የሥርዓተ-ፆታን እኩልነት በመንደፍ የትምህርት ፕሮግራሞችን እና የሥርዓተ-ትምህርት ቀረጻ ላይ ትኩረት በማድረግ ሴቶች የአቪዬሽን ዘርፍ እንዲገቡ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል። በሌላ በኩል ሴቶች ወደ አቪዬሽን ዘርፍ እንዳይገቡ የሚከለክሉትን ተግዳሮቶች በጥናት መለየትና መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ክብርት ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

በኮሜሳ የስርዓተ ጾታ እና ማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ቢያትሪስ ሀሙሴንዴ በበኩላቸው
በአህጉራችን የአቪዬሽን ዘርፉን ለማሳደግ በምስራቅ አፍሪካ፣ ደቡባዊ አፍሪካ እና በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ የአየር ትራንስፖርት ልማቱን በመደገፍ ላይ እንደሚገኝና ሴቶች በዚሁ ዘርፍ እንዲሳተፉና ዘላቂነት ያለው የአየር ትራንስፖርት እንዲኖር ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ መድረክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካሄድ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለደረገው ከፍተኛ ጥረት አመስግነዋል።

ፕሮግራሙ መጠናቀቁን ተከትሎ ተሳታፊዎች በመነንና በሚኒሊክ መሰናዶ ት/ቤቶች ጉብኝት ተደርጓል። በዚሁ ጊዜም፥ ሴት ተማሪዎች የአቪዬሽን ዘርፍን እንዲቀላቀሉና ዓላማ አድርገው እንዲተጉ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሴት አብራሪ እና ሴት ግራውንድ ቴክኒሻን በተገኙበት የማነቃቃትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ተካሂዷል።

 

Please follow and like us: