“ዘላቂ የሀገር ልማትና እድገት ለማምጣት ወጣቱ ጊዜውን በአግባቡ ሊጠቀም ይገባል” – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

ቀጣይነት ያለው የሀገር ልማትና እድገት ለማምጣት ወጣቱ ትውልድ ወርቃማ ጊዜውን በአግባቡ ሊጠቀም ይገባል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ፡፡

14ኛው የኦሮሚያ ክልላዊ የወጣቶች ኮንፈረንስ ማጠቃለያ እና የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር “ወጣት የለውጥ ሀይል፣ የሀገር ምሰሶ እና የነገ ተስፋ ነው!” በሚል መሪ ቃል በአዳማ ከተማ ገልማ አባ ገዳ አዳራሸ እየተካሄደ ነው። ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኮንፈረንሱ ባደረጉት ንግግር ÷ በሀገሪቱ የተገኙ ኢኮኖሚያዊ፣ የፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ለውጦችን ለማስቀጠል የወጣቶች ተሳትፎ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በዚህም ወጣቶች ከተለያዩ አልባሌ ድርጊቶች በመራቅና ያላቸውን አቅም በመጠቀም ለሀገራዊ እድገት እና ብልፅግና የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ወጣቶች በየአካባቢው ግጭቶችን በመፍታት ሰላም የሰፈነባት ሀገርን በመገንባቱ ረገድም ሚናቸው የጎላ መሆኑን በማንሳት በሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰፊ ትኩረት እየሰተሰጠው መምጣቱን ያወሱት ክብርት ሚኒስትሯ÷ በዚህም የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ዘንድሮ በሚከናወነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች ያላቸውን አቅምና እውቀት ተጠቅመው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም አፅንኦት ሰጥተዋል ።

የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ማቲዎስ ሰቦቃ በበኩላቸው÷ ወጣቶች ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቅርብ መሆናቸውን በመግለፅ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሀገር ለውጥ መስራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። በኮንፈረንሱ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀት አመራሮችን ጨምሮ ከሁሉም ኦሮሚያ አካባቢዎች የተወጣጡ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።

 

Please follow and like us: