ፎረሙ የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታትና የተቋቋመበትንም ዓላማ ማሳካት እንዲችል በጋራ መረባረብ ይገባል – አቶ ሙሉጌታ እሸቱ

ፎረሙ የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታትና የተቋቋመበትንም ዓላማ ማሳካት እንዲችል በጋራ መረባረብ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ እሸቱ ገለጹ።

7ኛው ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ፎረም መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ እሸቱ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ አካል ጉዳተኞች ያሉባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት እንዲሁም በሁሉም መስኮች አቅማቸው እንዲገነባና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል መንግስት አበረታች እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ተቋማዊ በሆነ መልኩ የሚካተትበትንና ተፈጻሚ የሚሆንበትን አሰራር ከመዘርጋት ጎን ለጎንም በማህበር ተደራጅተው ሁለንተናዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር በጽናት እንዲታገሉ ምቹ መደላድል መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ የተያዙ እቅዶችን ለማሳለጥና ስኬታማ ለማድረግ እንዲያስችልም ከ2013 ዓ.ም ወዲህ ፎረም ተቋቁሞ ወደስራ መግባቱንና ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። ፎረሙ ያለፈውን አፈፃፀም በመፈተሽና የነበሩ ክፍተቶችን በማረም የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታትና የተቋቋመበትንም ዓላማ ማሳካት እንዲችል ሁሉም በባለቤትነት እና በተነሳሽነት ሊረባረብ እንደሚገባ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየሰራ ባለው የግንዛቤና አድቮኬሲ ስራም አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት እየተለወጠና ምላሽ ሰጪነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጹት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሳልፈው አህመዲን ናቸው፡፡

አቶ አሳልፈው እንዳሉት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበርም አካል ጉዳተኛ ማህበራት ተገቢውን የፋይናንስና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲያገኙ መመቻቸቱንና ይህም ማህበራቱ ከጠባቂነት አስተሳሰብ ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉና ጠንካራ ቁመና ላይ እንዲገኙ የበኩሉን እገዛ አድርጓል። በቀጣይም ከአካል ጉዳተኛ ማህበራትና በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ላይ ከሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት አካታችነትንና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ክትትልና ድጋፍ የበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

 

Please follow and like us: