የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሴክሬተሪ ጀነራል የስርዓተ ጾታ ጉዳይ ኃላፊ ሚስተር ክርስቲያን ኤፍ. ሰንደርስ እና ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሴክሬተሪ ጀነራል የስርዓተ ጾታ ጉዳይ ኃላፊ ሚስተር ክርስቲያን ኤፍ. ሰንደርስ እና ልዑካን ቡድን ጋር በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ።

በውይይቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደሀገር ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችንና ትንኮሳዎችን ለመከላከል፣ የሴቶችን መብት ለማስከበር፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥና ሴቶችን ለማብቃት በርካታ ስራ እየተሰራ መሆኑን በሰፊው አብራርተዋል። ሴቶችን ከጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ከመከላከልና መብታቸውን ከማስከበር አኳያ በተለይ ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራት በመቻሉ አበረታች ውጤት መምጣቱንም ገልጸዋል። በዚህም ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ለሽልማት መብቃቷንና ለተገኘው ስኬትም የአለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል፤ ለተደረገው ድጋፍም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

ኮቪድን በተከሰተበትና በተለያዩ ጊዜያትም ግጭትና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ባጋጠመበት ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ለመደገፍና ለማቋቋም መንግስት ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱንና አሁንም ሰፊ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የተጀመሩ ስራዎችን ለማስቀጠልም የአለም አቀፍ ተቋማት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሴክሬተሪ ጀነራል የስርዓተ ጾታ ጉዳይ ኃላፊ ሚስተር ክርስቲያን ኤፍ. ሰንደርስ በበኩላቸው ሴቶችን ከጥቃትና ትንኮሳ ለመከላከልና መብታቸውን ለማስከበር እንዲሁም ከግጭት ጋር በተያያዘ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍም በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆን የክትትል ስራዎችን በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል። በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሚሰራቸው ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል።

 

Please follow and like us: