“ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች በጎነትን በማስረጽና አብሮነትን በማጠናከር የዜግነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡና አሻራቸውን በተግባር ሊያኖሩ ይገባል” – የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

የ2016 ዓ.ም የወጣቶች የክረምት ወራት ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መክፈቻ መርሀ-ግብር በደቡብ ኢትዮጵያ አርባምንጭ ከተማ ተካሄደ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለፁት፤ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለዉ እንደ ስሙ በበጎ ልቦና ከንፁህ ልብ፤ ከንፁህ ህሊና ከንጹህ ፍቅርና ፍጹም መልካምነት የመነጨ በነጻ የሚሰጥ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰዎች ውስጣቸው ከሚሰማቸው ሰብዓዊ አመለካከት በመነሳት ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ልማትና ለአካባቢ ደህንነት ነፃ ጊዚያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና በጎ አመለካከታቸውን ተግባር ላይ የሚያውሉበት በምላሹም ከማህበረሰቡ ጠቃሚ ዕሴቶች፣ የህይወት ክህሎት፣ ልምድና ባህሎችን የሚቀስሙበትም ነው ብለዋል።

በዕለቱ ክብርት ሚኒስትር ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የ2016 ዓ.ም ወሰን ተሻጋሪ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አርማና መለያ ባንዲራ አስረክበዋል። ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በጎነትን በማስረጽና አብሮነትን በማጠናከር የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና አሻራቸውን በተግባር እንዲያኖሩም ጥሪ አቅርበዋል። በሌላ በኩል ወጣቶቹ ለበጎ ስራ በተንቀሳቀሱበት አካባቢ ሁሉ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጎነትና አብሮነትን ለማጠናከር እንደሀገር ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ሁሉ የበኩሉን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልፀዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሠ (ዶ/ር) በበኩላቸው በጎነት በኢትዮጵያውያን ህሊና ውስጥ ያለ ነገር ግን በአግባቡ አውጥተን ያልተጠቀምንበት ትልቅ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው ከለውጡ ማግስት ወዲህ ግን በጎፍቃድን በሰው ተኮር ስራዎች ላይ በማዋል ብዙ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን መድረስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

አክለውም በክልሉ ወጣቶቹ ያስጀመሩትን የበጎ ፈቃድ ስራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የደም ልገሳ እና ሌሎች የበጎ ፈቃድ ተግባራት እንደሚከናወን ተጠቁሟል።

 

Please follow and like us: