ኢትዮጵያ ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ለመከላከል በሰራችው ስራ እውቅና አገኘች፡፡

(ሀምሌ 5/2016) ኢትዮጵያ ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ለመከላከል በሰራችው ስራ በተባበሩት መንግስታት ስነ- ህዝብ ሽልማት ላይ እውቅና አገኘች፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የተቋቋመውን ጥምረት ወክለው በተባበሩት መንግስታት ዋና መስሪያ ቤት ኒውዮርክ ተገኝተው ሽልማቱን ተቀብለዋል፡፡ ሚኒስትሯ ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የወሰዳችውን የህግ፣ የፖሊሲና የፕሮግራም እርምጃዎች አብራርተዋል። ይህ አለም አቀፍ አውቅናና ሽልማት መንግስት ለስርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን ማብቃት ያለውን ቁርጠኝነት የበለጠ የሚያጠናክር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በሽልማቱ ላይም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመራሮችና ሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራትና አለም አቀፍ ድርጅቶች ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የተቋቋመው ጥምረት እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በጥምረቱ ውስጥ የመንግስት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማት፣ የሀይማኖት ተቋማት ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ጥምረቱ በሴቶችና ማሀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ሲሆን ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ በፖሊሲ፣ ግንዛቤ በመፍጠር እንዲሁም መረጃን ተደራሽ በማድረግ ስኬታማ ሆኗል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ስነ- ህዝብ ሽልማት እ.ኤ.አ በ1981 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የተመሰረተ ሲሆን በየአመቱ በስነ ህዝብና ስነ -ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ልዪ አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ይሰጣል፡፡

 

Please follow and like us: